ግሎባል አሊያንስ ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ

60

ሰቆጣ፣  የካቲት 29/2014-(ኢዜአ) ግሎባል አሊያንስ በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ፣ አልባሳትና ፍራሽ ድጋፍ አደረገ።

የግሎባል አሊያንስ በኢትዮጵያ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ አምሃ መኮንን በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት ግሎባል አሊያንስ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ ነው።

በአፋርና አማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከዚህ ቀደም  67 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውሰዋል።

በዛሬው ዕለትም በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ምግብና አልባሳትና ፍራሽ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።ድጋፉ የበቆሎ ዱቄትና  የህፃናት አልሚ ምግብ  እንዲሁም ብርድ ልብስና ፍራሽ ያካተተ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖች መልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የአማራ ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፋንታ በበኩላቸው ድጋፉ በሽብር ቡድኑ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር የሚያቃልል መሆኑን ተናግረዋል።

ግሎባል አሊያንስ በችግር ላይ ላሉ ዜጎች እያደረገ ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበው "የአማራ ልማት ማህበርም በተለያየ ጊዜ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በፈፀመው ወረራ በርካታ ወገኖች ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

በወረራው ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ከቄያቸው ተፈናቅለው በሰቆጣና ፅፅቃ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ግሎባል አሊያንስ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር ለማቃለል  ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ለተፈናቀሉ ወገኖች የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም