በቅራኔ ላይ የተመሰረቱ ትርክቶችን ለማስተካከል በመርህና እውቅት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ለመፍጠር እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
በቅራኔ ላይ የተመሰረቱ ትርክቶችን ለማስተካከል በመርህና እውቅት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ለመፍጠር እንሰራለን
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቅራኔ ላይ የተመሰረቱና የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተካከል በመርህ፣ መረጃና እውቅት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የዜጎች መብት ማስተባበሪያ ድርጅት ገለጸ።
የኢትዮጵያ የዜጎች መብት ማስተባበሪያ ድርጅት ከ10 ዓመት በፊት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የተመሰረተ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ በ2013 ዓ.ም በሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሞገስ በቀለ፤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተካከል በመርህ፣ በእውቅትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ትምህርት የመስጠት ዓላማ ይዞ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ከመንግስት፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ለመምከር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከሚያራርቁ ይልቅ አንድ የሚያደርጉ በርካታ እሴቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ ድርጅቱ ፍቅርና አብሮነትን እንዲሁም አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት የድርሻውን ለመወጣት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ በልዩነቶች ላይ ብቻ ያተኮሩ የተለያዩ ትርክቶችም ስላሉ ለማስተካከል በመርህና እውነት ላይ የተመሰረተ ስራ ለማከናወን ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር እርቁ ይመር፤ በኢትዮጵያ የቆዩ ማህበረሰባዊ እሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየተሸረሸረ በመምጣታቸው በፅኑ መሰረት ላይ እንዲዘልቁ ለማስቻል ድርጅቱ በትኩረት ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።