ቤተ እምነቶች ለአገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ቤተ እምነቶች ለአገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል
የካቲት 29/2014/ኢዜአ/ ቤተ እምነቶች ለአገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የተለያዩ የእምነት ተቋማት የኃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡
ኃይማኖቶች የአስተምህሯቸው መሰረት የሰው ልጆች አብሮነት በመሆኑ በሕዝቦች ዘንድ ሰላምና አንድነትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይታመናል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች እንደሚሉት፣ ቤተ እምነቶች ልዩነቶችን አቻችሎ ለሰላምና አንድነት መትጋት ይኖርባቸዋል።
የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት የሚቻለው የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት አገር መፍጠር ሲቻል መሆኑንም ይናገራሉ አባቶቹ።
ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም የኃይማኖት አባቶች በቤተ እምነቶቻቸው በኩል ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ይጠይቃሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃ ዋና መምሪያ ኃላፊ መላከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ ''ኢትዮጵያ የአማኞች አገር ናት'' ይላሉ።
ይህም በመሆኑ ሁሉም ቤተ እምነቶች ሰለ ሰላምና አንድነት አስፈላጊነት በየእለቱ ለተከታዮቻቸው ሊያስተምሩ ይገባል ብለዋል።
የእምነቱ ተከታዮችም ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎችንና ኃይማኖታዊ ትዕዛዛቱን መተግበር እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ።
ከሁሉም በላይ ሰላም ከራስ የሚጀምር በመሆኑ የሰላምን 'አምላካዊ ቃል' አክብሮና ተግብሮ ለሰላምና አንድነት ሁሉም የራሱን ሚና ማበርከት እንደሚገባውም ተናግረዋል።
ሌላው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባልና የሰላምና ዕርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሃመድ ሲራጅም እንዲሁ በየቤተ እምነቱ የሰላም አስፈላጊነት በስፋት ሊሰበክ ይገባል ይላሉ።
አማኞችም በሚከተሉት ኃይማኖት ያለውን የሰላም አስተምህሮና ትዕዛዝ በመከተል ለአገር ሰላም አስተዋፆ ማበርከት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
"በተከፋፈልንና በተለያየን ቁጥር ለጠላቶቻችን በር እየከፈትን ነው" ያሉት ሼህ መሃመድ የቋንቋም ሆነ ሌሎች ልዩነቶችን አቻችሎ፤ ተከባብሮና ተዋዶ መኖር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው ''በሰው ልጆች ዘንድ በተለያየ መልኩ የሚገለጹ ልዩነቶች ከፍጥረት ጀምሮ ያሉና አምላካዊ ናቸው'' ይላሉ።
እነዚህን ልዩነቶች እንደመከፋፈያና መለያያ ከመጠቀም ይልቅ የተፈጥሮ ህግ መሆኑን አውቆና አክብሮ በሰላምና በአንድነት መኖር ተገቢና የፈጣሪ ትዕዛዝ መሆኑን ያብራራሉ።
ፓስተር ጻድቁ በመሆኑም ጥቃቅን ልዩነቶችን አቻችሎ ለአገር ሰላምና አንድነት መትጋት ይገባል ሲሉም ይመክራሉ።
ኢትዮጵያውያንም እነዚህን አመለካከቶች ወደ ጎን በመተው ልዩነቶችን በማክበርና እውቅና በመስጠት ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።