ቀጥታ፡

ለባሌ ዞን ድርቅ ተጎጂዎች የምግብ እህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ ተደረገ

ጎባ የካቲት 29/2014 (ኢዜአ)--- የለገ ጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደርና የአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ እህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ አደረጉ ፡፡

አስተዳደሩና ኮሌጁ ያደረጉት ድጋፍ 1ሺህ 400 ኩንታል የምግብ እህልና 2ሺህ 110 እስር ሳር ነው ፡፡

የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድኑር ሙሄና የአጋርፋ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ጫላ ፈዬራ ለባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሀም ሀይሌና ለአባ ገዳዎች ድጋፉን ዛሬ አስረክበዋል።

የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድኑር ሙሄ በወቅቱ እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩ ለዞኑ ድርቅ ተጎጂዎች ያደረገው ድጋፍ 1ሺህ 200 ኩንታል የምግብ እህልና 1ሺህ 415  እስር ሳር ነው፡፡

የከተማው ባለሀብቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል ።

በአጋርፋ ግብርና፣ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በኩል 200 ኩንታል የምግብ እህልና 700 እስር ሳር ድጋፍ መደረጉን  የገለጹት ደግሞ የኮሌጁ ዲን ዶክተር ጫላ ፈዬራ ናቸው።

ዶክተር ጫላ እንዳሉት ኮሌጁ ለድርቅ ተጎጂዎች ከሚያደርገው የዕለት ደራሽ ድጋፍ በተጓዳኝ የአርሶ አደሩን ግብርና በሚያዘምኑና የድርቅ ተጋላጭነትን በሚቀንሱ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ላይ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ሀይሌ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩና ኮሌጁ ላደረጉት ድጋፍ በዞኑ በድርቅ ተጎጂዎች ስም አመስግነዋል፡፡

ህብረተሰቡና ተቋማት ችግሩ እስኪያልፍ ድረስ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በባሌ ዞን ድርቁ ከተከሰተ  ጊዜ ጀምሮ ከ17ሺ ኩንታል በላይ እህልና 15ሺ 370 እስር የእንሰሳት መኖ  መከፋፈሉን የዞኑ የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም