ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ክብርና ህልውና ሲሉ ጀብድ የፈጸሙ ጀግና ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታላቅ ክብር ይገባቸዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29/2014(ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ክብርና ህልውና ሲሉ ጀብድ የፈጸሙ ጀግና ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ46ኛ በዓለም ደግሞ ለ111ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

በአገር መከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እለቱን ለማክበር በነበረው መርሃ ግብር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም ለኢትዮጵያ ክብርና ህልውና ሲሉ ጀብድ የፈጸሙ ጀግና ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

"በሁሉም የጦር ግንባሮች ጀብድ ፈጽማችሁ አገራችሁን ለታደጋችሁ ሴቶች ክብርና ምስጋናችን ይድረሳችሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚገጥማቸውን ሁሉ ፈተና በመቋቋም አርዓያነት ያለው ተግባር ፈጽመዋል ያሉት ፕሬዝዳንቷ ለወደፊትም በእነርሱ መሰል ጀግኖች ድርብ መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ክብሯ ተጠብቆ ትቀጥላለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች የመከራ ተሸካሚ ብቻ መሆን የለባቸውም ያሉት ፕሬዝዳንቷ የሐሳብና መፍትሄ ባለቤቶች በመሆናቸው በሁሉም መስክ የላቀ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።    

የመከላከያ ሴት ወታደሮችን በተሻለ መልኩ ለአመራርነት በማብቃት ቁልፍ ውሳኔዎች ላይ ትርጉም ባለው መልኩ ተሳትፈው ለአገራቸው የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

የመከላከያ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ጥሩዬ አሰፌ በበኩላቸው፤ ሴቶች ለአገራቸውና ለህዝባቸው ሲሉ በርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ ታሪክ መስራታቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት የኢትዮጵያን ህልውና በማስከበር ሂደት የነበራቸው የላቀ አፈጻጸም በታሪክ ሲታወስ የሚኖር መሆኑን ገልጸዋል።  

በህልውና ዘመቻው ታላቅ ጀብድ የፈጸሙ ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት እለቱን በማስመልከት በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው መካከል አስተያየታቸውን የሰጡ የሰራዊቱ አባላት ለአገር ክብር ሲባል በፈጸሙት ታላቅ ጀብድ ኩራት የሚሰማቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያን ህልውና በማስጠበቅ እንደቀደመው ሁሉ ደማቅ ታሪክ ለመጻፍ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ሌሎች ሴቶችም ወደ መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀል ለአገራቸው እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ "እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ!!" በሚል እንዲሁም በአገር መከላከያ ሰራዊት "የአገራችን ሰላም በሴቷ ተጋድሎ ህያውነት ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም