አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ፕሮግራም የምዘና ውድድር በኦሮሚያ ክልል አሸናፊነት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ፕሮግራም የምዘና ውድድር በኦሮሚያ ክልል አሸናፊነት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2010 6ኛው አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ፕሮግራም የምዘና ውድድር በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በጋራ ያዘጋጁት የምዘና ውድድር ከነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ፣ አሰላና ቢሾፍቱ ከተሞች ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል። በምዘና ውድድሩ ላይ ሰባት ክልሎች እና 2ቱም የከተማ አስተዳደሮች ተሳትፈዋል። በኦሎምፒክና ፓራኦሎምፒክ ስፖርቶች በአጠቃላይ 1 ሺህ 723 ወንዶች እና 1 ሺህ 113 ሴቶች በድምሩ 2 ሺህ 830 ስፖርተኞች በምዘናው መካፈላቸውን ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ውድድሩ ትናንት ሲጠናቀቅ ኦሮሚያ ክልል በኦሎምፒክና ፓራኦሎምፒክ ውድድሮች የአጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫ ተረክቧል። በውድድሩ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ስልጠና ደካማና ጠንካራ ጎን መገምግሙ ተገልጿል። በዚሁ መሰረት ሰባት የሚሆኑ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት እና ክለቦች በምዘናው ውድድሩ የተሳተፉ 122 ታዳጊዎችን መልምለው ስልጠና እንደሚሰጡም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በውድድሩ መዝጊያ ቀን በሁለቱም ጾታ በተደረገው እግር ኳስ የምዘና ውድድር በወንዶች ኦሮሚያ ክልል የወርቅ፣ የአማራ ክልል የብር፣ የደቡብ ክልል የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በሴቶች ደግሞ የደቡብ ክልል የወርቅ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብርና የአማራ ክልል የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። የኦሮሚያ ክልል በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የምዘና ውድድር ለማስተናገድ ፈቃደኛ በመሆኑ እና በሶስቱ ከተሞች ውድድሩ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሁሉንም የልዑካን ቡድን በፍቅርና በአንድነት አስተናግዷል። በተለይ ደግሞ ወጣቱ በሁሉም የስፖርት ሜዳዎች በመገኘት ድጋፉን በመስጠት እንዲሁም ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ የፀጥታ አካላትን በማገዝ ያደረጉት አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ምስጋናውን አቅርቧል። አምስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ፕሮጀክት የምዘና ውድድር ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል ሃዋሳ ከተማ የተካሄደ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።