የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ማስተማር ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ማስተማር ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ የካቲት 29/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በስፔስ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው።
በዘርፉ ለማስተማር ዩኒቨርሲቲው ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ በስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ የማብሰሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላትም በዘርፉ የተቀረጸውን ሥርዓተ ትምህርት ለኢንስቲትዩቱ በዛሬው እለት አስረክበዋል።
በመጀመሪያው ዙር በሁለተኛ ዲግሪና ሦስተኛ ዲግሪ 13 ተማሪዎችን ይቀበላል ተብሏል።
በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ የሚመረቁ ባለሙያዎች በራሳቸው አቅም ሳተላይት መገጣጠም፣ ማምረት እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላን(ድሮኖችን) ዲዛይን ማድረግና ማምረት ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ፤ ዩኒቨርሲቲው ከኢንስቲትዩቱ ጋር በአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው ስፔስ ኢንጂነሪንግ አንዱ የትብብር መስክ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲው በትጋት ይሰራል ብለዋል።
ስፔስ ኢንጂነሪንግና ኤሮኖቲካል እንጂነሪንግ በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በሦስተኛ ዲግሪ ደግሞ ኤሮስፔስ እንጂነሪንግ ባለሙያዎችን ለማፍራት የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ መካሄዱን አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ በዘርፉ በቂ ባለሙያ ለማፍራት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይሽሩን ዓለማየሁ፤ ኢትዮጵያ ከስፔሱ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በስፔስ ኢንጂነሪንግ አሁንም የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ጠቁመው፤ ይህም በሥራው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
ከመከላከያ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከራሱ ከኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች እውቀትና ልምዳቸውን ለተማሪዎቹ እንደሚያካፍሉም ነው ዶክተር ይሽሩን ያስረዱት።
ከውጭ ደግሞ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጋበዙ ባለሙያዎች እውቀታቸውን እንዲያጋሩ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ ብለዋል።