ቀጥታ፡

የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር ለማስፈጸም ዓብይና ንዑሳን ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 29/2014(ኢዜአ) አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር ለማስፈጸም ዓብይና ንዑሳን ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ቤተክርስቲያኗ አስታወቀች።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ሥርዓተ ቀብር የፊታችን እሁድ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገልጿል።

የብጹዕነታቸውን ስርዓተ ቀብር ዝርዝር መርሃ ግብር አስመልከቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።መግለጫውን የሰጡት በቤተክርስቲያኗ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸኃፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፤ ብጹዕነታቸው ከዚህ ዓለም በድካም ማረፋቸው ከተሰማ ጀምሮ ስርዓተ ቀብራቸውን ለማስፈጸም የተለያዩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የስርዓተ ጸሎት፣ የፕሮቶኮልና እንግዳ ተቀባይ፣ የቀብር አስፈፃሚ፣ የመርሃ ግብር አዘጋጅና ሚዲያ፣ የበጀትና ወጪ ኮሚቴዎችን ጨምሮ 12 ዓብይና አምስት ንዑሳን ኮሚቴዎች ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት።

በመግለጫቸው አክለውም ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ከ3 እስከ 7 ሰዓት ከ45 የሚቆይ የአስክሬን ሽኝት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በመስቀል አደባባይ በሚካሄደው የሽኝት መርሃ ግብርም የእህት ዓብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ይገኛሉ ብለዋል።

ከመስቀል አደባባይ የአስከሬን ሽኝት በኋላም በመንበረ ፓትሪያርክ ግቢ 'የፀሎተ ወንጌል ድርሳን' እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ጸሎተ ወንጌሉ ከተጠናቀቀ በኋላም ክቡር አስክሬናቸው ታጅቦ 'ለስብኃተ ማህሌት' ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን እንደሚሄድ አንስተዋል።

እሁድ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ከጠዋቱ ከ2፡30 ጀምሮ በሚከናወን መርሃ ግብር የብፁዕነታቸው ክቡር አስክሬን ያርፋል ነው ያሉት።

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ሌሎች የክብር እንግዶች ይገኛሉ ብለዋል።

በቀድሞ ጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ-ታቦር አውራጃ በዓለታ ወረዳ አርጊት ኪዳንምህረት በ1930 ዓ.ም የተወለዱት ብፁዑ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ84 ዓመታቸው የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም