ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ በኩል ከህግ ማሻሻያ ጀምሮ በርካታ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል

የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ በኩል ከህግ ማሻሻያ ጀምሮ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ገለጹ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፤ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የፓርላማ ሴቶች አባላት ቁጥር አራት እንደነበር አስታውሰው የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ ትግል መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደትም የህግ ማዕቀፍ በማሻሻል፣ ደጋፊ ፖሊሲዎችን በመቅረፅ እና የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የሴቶችን እኩልነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድም ከህግ ማሻሻል ጀምሮ በርካታ የማስተካከያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ቀላል በማይባል መልኩ መሻሻል ታይቶበታል ያሉት ፕሬዝዳንቷ ታሪካዊ ለውጥም ተመዝግቦበታል ብለዋል።

በተለይም በአስፈጻሚው የመንግስት መዋቅር ሴቶች ያላቸው ሚና ባለፉት ሶስት ዓመታት ማደጉን ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።

የአገሪቷ ርዕሰ ብሔር እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሴት ሆነው መሾማቸውም ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በሴቶች የሚመሩ ተቋማትና ሌሎችም የሃላፊነት ቦታዎች በፈተና የታጀቡ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ያደጉ አገሮችም ቢሆኑ ገና ያላሸነፉት መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶች ሙሉ ተሳትፎ ተቋሞችን ለመገንባት፣ ሰላም ለማምጣትና ልማት ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው ሴት አመራሮች ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወርቅነሽ በቀለ፤ የስርአተ ጾታ እኩልነትን ለማክበርና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አድሎ ለማስቀረት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ በፍርድ ሂደት ወደ ፍርድ ቤት ለአገልግሎት የሚመጡ ሴቶች ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ተሟጋችነት ያለው የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

ድጋፍ ቢደረግላቸው ለራሳቸው፣ ለአካባቢያቸው ብሎም ለአገር የሚጠቅም እውቀት እና ችሎታ ያላቸው በርካታ ሴቶች መኖራቸውን የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

በተለይ በሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በመሆን ስልጠና እና መሰል ድጋፎችን በመስጠት የአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ሴቶች በየትኛውም የሃላፊነት ቦታ ላይ ቢቀመጡ ሃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት እና ውጤታማ ለመሆን የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለም አንስተዋል።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም