ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ስናከብር በችግር ላይ የሚገኙ ሴቶችን በዘላቂነት በማቋቋም መሆን አለበት

የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ስናከብር በችግር ላይ የሚገኙ ሴቶችን በዘላቂነት በማቋቋም መሆን አለበት ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ፡፡
በዓለም ለ111ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

እለቱን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራትን እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሴቶች አደረጃጀቶች ተቀናጅተው የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሰሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ይሁንና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት በተለይ ሴቶች ይበልጥ ተጎጂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በርካታ ሴቶች ለጾታዊና አከላዊ ጥቃት መዳረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ስናከብር በችግር ውስጥ የሚገኙ እናትና እህቶቻችንን በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፍ በማድረግ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ከየካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ ማድረግን ዓላማ ያደረገ አገር አቀፍ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር እቅድ በማውጣት ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆን እየደገፉ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

የአንድ ማዕከል አገልግሎትና የተሃድሶ ስራዎች ደግሞ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በዚህም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በቀላሉ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም