ባለፉት 6 ወራት ሀዋሳን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

66

ሀዋሳ የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ሀዋሳ ከተማን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የከተማዋ  ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ገለጸ።

የሀዋሳ ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ዳርጊቱ ጫሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማዋ በአገር ውስጥና በውጭ ጎብኚዎች ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ከመሆን ባለፈ የንግድና የስብሰባ ማዕከል እየሆነች መጥታለች።

ሀላፊዋ እንዳሉት ባለፉት 2 ዓመታት በኮቪድ-19 እና በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረውን የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመቀየር በተሰራው የገጽታ ግንባታ ሥራ ለውጥ እየታየ ነው።

ለእዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከተማዋን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ገቢው በከተማዋ ከሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰበሰበ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር 25 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል "የከተማዋ መለያ የሆነው የሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻው በተገቢው ያልለማና ያልተጠቀምንበት ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ነው" ያሉት ሃላፊዋ፣ የሐይቁን ዳርቻ ለማልማት የ10 ዓመት ፕሮጀክት መቀረጹን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ባህላዊ እሴቶችን በሚያሳይ መልኩ የሚገነባ ሲሆን የሳይክል መወዳደሪያ ስፍራ፣ የዋና መዋኛና ሌሎች መዝናኛዎችም ማካተቱን አስታውቀዋል።

የግንባታ ስራውም በቅርቡ እንደሚጀመርና ከ3ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጠር ወይዘሮ ዳርጊቱ ተናግረዋል።

ከሐይቁ ዳርቻ በተጨማሪ የታቦር ተራራን የማልማት ፕሮጀክት የዲዛይን ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን ስራውም ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚወስድ ነው የተናገሩት።

ግንባታው ሲካሄድ የቆየው የቱሪስት መረጃ ማዕከል በአሁኑ ወቅት 95 ከመቶ መጠናቀቁን ጠቁመው፣ "በቅርቡ ሥራ ሲጀምር ቱሪስቶች ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል" ብለዋል።

ማዕከሉ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባና በከተማዋ መግቢያ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሃዋሳ ከተማ 16 ባለኮከብ ሄቶሎችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን በከተማዋ የሚከናወነው የአረንጓዴ ልማት ሥራና በከታታይ የተካሄዱ የከተሞች ውድድር ሀዋሳን ተሸላሚ ከማድረግ ባለፈ የቱሪስት ዓይን ማረፊያ አድርጓታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም