ቀጥታ፡

በሽሬ እንዳስላሴና ጅማ አባቡና መካከል ነገ ጨዋታ ይደረጋል

አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2010 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድገውን ሶስተኛ ክለብ ለመለየት ነገ በሃዋሳ ስታዲየም ሽሬ እንዳስላሴና ጅማ አባቡና ጨዋታ ያደርጋሉ። በ2010 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ውድድር በምድብ 'ሀ' ባህርዳር ከተማ በምድብ 'ለ' ደቡብ ፖሊስ በአንድነት ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  ለመሳተፋ ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚገባውን ሶስተኛ ክለብ የሚወስነው ጨዋታ ነገ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ በሃዋሳ ስታዲየም በሽሬ እንዳስላሴና ጅማ አባቡና መካከል ይደረጋል። ሽሬ እንደስላሴ በምድብ 'ሀ'፣ ጅማ አባቡና  በምድብ 'ለ' ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመግባት እርስ በእርስ ይፋለማሉ። የጨዋታው አሸናፊ ክለብ በመጪው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ይቀላቀላል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጀመሪያ በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል ቢባልም ስታዲየሙ በእድሳት ላይ በመሆኑ ወደ ሃዋሳ ስታዲየም መቀየሩ ይታወቃል። በሌላ በኩል በባህር ዳር ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ መካከል የሚደረገው የዋንጫ ጨዋታ ነገ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይደረጋል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ አርባምንጭ ከተማና ወልዲያ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም