አገሪቱ የሚያጋጥሟትን ችግሮች ለመፍታት የውይይት እሴት ሊዳብር ይገባል

71

የካቲት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)  አገሪቱ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የውይይት እሴት ሊዳብር እንደሚገባ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

"የውይይት እሴት ባህልን ለማዳበር የሃይማኖት ተቋማት አስተዋጽኦ" በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት  ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ የውይይት እሴቶች መጠቀም አለበት።

በተለይም አገሪቱ አሁን ላይ የሚያጋጥሟትን ችግሮች ለመፍታት ውይይት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው ውይይቶችን በማጠናከር መግባባት መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መላከ ሕይወት ቆሞስ ሃይለ እየሱስ ሰይፈ፤ ቤተ-እምነቶች የውይይት ባህል እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ ብለዋል።

"የተለያዩ ሃይማኖት፣ ባህልና ቋንቋ ቢኖረንም፤ ሁሉም የእምነት ተቋማት እርስበርስ የመነጋገርና የመወያየት ባሕላችን እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለባቸው ያሉት ደግሞ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል ሐጂ ጀሚል አማን ናቸው።

ችግሮች መልካቸው ይቀያየራል እንጂ ሁልጊዜ ይኖራሉ ያሉት ደግሞ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የጉባኤው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ቄስ ለገሰ ጀባት ናቸው።

ይህም ሆኖ ውይይቶችን ማድረግ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያግዛል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እስካሁን በአዲስ አበባ ስድስት ክፍለ ከተሞች  የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ እያደረገ ነው።

በመድረኩ የውይይትን ጠቃሚነት በሃይማኖታዊ አስተምህሮ አካቶ ከመሥራት አኳያ የእምነት ተቋማትን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም