የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥና ሴቶች ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥና ሴቶች ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

የካቲት 28/2014 /ኢዜአ/ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥና ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሴቶች ቀን (March 8) በጃፓን ኤምባሲ ዛሬ ተከብሯል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቷል።
ጎን ለጎንም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ሁሉንም አይነት ጥቃቶችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የሴቶች ጉዳይ በሁሉም ዘርፎችና ተቋማት ጉዳይ ውስጥ እንዲካተትና መካተታቸውን በመደበኛነት የመከታተል ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን አብራርው፤ አነዚህም ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።
የሴቶችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር በመንግሥት ብቻ የሚከወን ተግባር አለመሆኑን ጠቅሰው የሁሉም ተቋማትና ግለሰቦች ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ቅንጅታዊ አሰራርና የባለ ብዙወገን ትብብር መጠናከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የሴቶች ጉዳይ በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዲሰማ ተቋማት ከሚያደርጉት ጥረት በተጓዳኝ ሴቶች በአንድነት ድምጻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሴቶች እኩልነትን ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት በተደረጉ ጥረቶች የተገኙ ውጤቶች የጋራ ውጤቶች መሆናቸውን አንስተው መልካም ተሞክሮዎችም መለዋወጥ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት የዜጎችን በተለይም የሴቶችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት መከበርን የሚያደርጋቸውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።