ኢዜአ በህልውና ዘመቻው በሚዲያው ዘርፍ የላቀ ሚና ነበረው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በህልውና ዘመቻው በሚዲያው ዘርፍ የላቀ ሚና ነበረው
አዲስ አበባ የካቲት 28/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ በህልውና ዘመቻው በሚዲያው ዘርፍ የላቀ ሚና እንደነበረው የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።
ኢዜአ ፈጣንና ተአማኒ መረጃ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በህዝቦች ዘንድ ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት የሚያደርጉ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ1934 ዓ.ም ተመስርቶ ላለፉት 80 ዓመታት የኢትዮጵያ ብቸኛ የዜና ምንጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
የተቋሙን 80ኛ ዓመት ምስረታ በዓል በማስመልከት ባለፈው ሳምንት አውደ ርእይ ተከፍቶ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።
በእለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስተ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አውደ ርእዩ ካለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ ለእይታ ክፍት በመሆኑ በርካታ ሰዎች እየጎበኙት ሲሆን በዛሬው እለትም ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጎብኝተውታል።
በምድር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴል ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ፤ አውደ ርእዩን ከጎበኙት መካከል ሲሆኑ ኢዜአ ታላቅ የአገር ባለውለታ መሆኑን አንስተዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ስጋት ደቅኖ የነበረውን አሸባሪው ህወሃት በመዋጋትና አገር የማዳን ዘመቻው /ኢዜአ/ በሚዲያው ዘርፍ የጎላ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።
ከምድረኃይል ጠቅላይ መምሪያ ለጉብኝት የመጡት ሻለቃ ገዳምነሽ እንዳለ፤ ኢዜአ የአገር ታሪክ ባለውለታ፣ የመረጃ አለኝታና የህዝብ ልሳን ሆኖ ያገለገለና እያገለገለ ያለ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቀጣይም በተለያዩ ኹነቶች መከበሩ የሚቀጥል ሲሆን አውደ ርእዩም ካለፈው አርብ ጀምሮ ለ7 ተከታታይ ቀናት ለእይታ ክፍት ይሆናል።