ቀጥታ፡

በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

አርባ ምንጭ፤ የካቲት 28/2014 (ኢዜአ).. በደቡብ ክልል በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ዘነበ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለፁት ትላንት ረፋድ ላይ ከአርባ ምንጭ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የፓርኩ ክፍል ላይ መጠነኛ ጪስ ይስተዋል ነበር።

ነፋሻማ አየርና ሙቀት እያየለ ሲመጣ ከሰዓት በኋላ የሰደድ እሳቱ መጠንም እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ትናንት ማምሻውን ከ12:00 ሰዓት ጀምሮ የአርባ ምንጭ ከተማ ሚሊሻ አባላትን በማስተባበር እሳቱን ለመቆጣጠር መሞከሩን ተናግረዋል ።

ከሌሉቱ ዘጠኝ ሰዓት እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስ ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ እና ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም የጋሞ ዞን ፓሊስ አባላትን፣ የከተማና ዙሪያ ወረዳ ሚሊሻዎችና የፓርኩን ስካውቶች በማስተባበርና 200 የሚሆን የሰው ኃይል በማሰማራት እሳቱን ለመቆጣጠር ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።

''በተደረገው ርብርብ በአሁኑ ወቅት የእሳት አደጋውን ማብረድ ችለናል'' ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ሌሊት አደጋውን ለመቆጣጠር ሲረባረቡ የነበሩ ግብረ ሃይሎችን በተመሳሳይ የሰው ኃይል በመተካት አልፎ አልፎ የሚታይ የእሳት አደጋን የማጥፋትና የቅኝት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አደጋው የተነሳው ተራራማ ስፍራ ላይ በመሆኑ ከሰው ኃይል በተጨማሪ የድሮን ቅኝት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የእሳት አደጋው መነሻ ከሰል ከሚያከስሉ እና የከብቶች ሳር ፍለጋ ከገቡ ሰዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምት እንዳለ ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም