ኢዜአ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞና አዳዲስ አሰራሮችን ጨምሮ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞና አዳዲስ አሰራሮችን ጨምሮ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት
የካቲት 28/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞና አዳዲስ አሰራሮችን ጨምሮ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ1934 ዓ.ም ተመሰርቶ ላለፉት 80 ዓመታት የዘለቀ ብቸኛ የዜና ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ አንጋፋና ታሪካዊ ተቋም ነው።
የተቋሙን 80ኛ ዓመት ምስረታ በማስመልከት በተዘጋጀው የፓናል ውይይትና አውደ ርእይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ተከፍቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት ኢዜአ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞና አዳዲስ አሰራሮችን ጨምሮ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ኢዜአ ለታሪክ የሚተላለፍ ስራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያን የሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
የህ/ተም/ቤት አባል አቡኔ አለምነው በሰጡት አስተያየት "ኢዜአ ትኩረት አድርጎ መስራት አለበት ብለን የምንወስደው 1ኛውና መሰረታዊ ጉዳይ ሀገርን ማሻገር ላይ ነው"ብለዋል፡፡
ሌላዋ የህ/ተም/ቤት አባል ቤተል መልካሙ በበኩላቸው "ኢዜአ አንጋፋ ሚዲያ እንደመሆኑ ዜናን በጥንቃቄ ማቅረብ እንዳለበትና ሌሎች ሚዲያዎች ከኢዜአ የሚማሩና ማሳያ መሆን ይጠበቅበታል።"ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
አክለውም የዜና ሽፋን በትልልቅ ከተሞች ብቻ መወሰን እንደሌለበትና ሩቅ ያሉትን ለአለም ለማሳወቅ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ተወስዶ ሊከናወን የታሰበው አገራዊ ምክክር ውጤት እንዲያመጣ የኢዜአ ሚና የላቀ መሆን እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል።
ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ አገርና ህዝብን ለማገልገል የጀመረው ጥረት እንዲሳካ የምክር ቤቱ ድጋፍና ክትትል እንደማይለየው አረጋግጠዋል።