ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው
የካቲት 27/2014/ኢዜአ/የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
በህገ-ወጥ መልኩ በአቋራጭ ለመክበር በሚጥሩ አካላት ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት በስግብግብ ነጋዴዎችና በአቋራጭ ለመክበር በሚጥሩ ደላላዎች አማካኝነት አላስፈላጊ የኑሮ ጫና በህዝብ ላይ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
"በመሆኑም ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመቆጣጠርና በመከላከል በህዝባችን ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ርብርባችን ይቀጥላል" ብለዋል ከንቲባዋ።
ህዝብን ማንገላታትና ለችግር ማጋለጥ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸው፤ ይህን ህገ-ወጥ ድርጊት በፍጥነት ማስቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለማቃለል ቁጥጥር እንዲሁም አማራጭ ገበያዎችን እና ምርት ለህብረተሰቡ ማድረስ የሚያስችሉ ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ግብረ-ኃይል በማቋቋም በተደረገ እንቅስቃሴም ዘይት ወደ ሌላ ቦታ ለማሸሽ የተደረጉ ጥረቶችን ማክሸፍ መቻሉን ጠቁመዋል።
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች የተከፈቱ የእሁድ ገበያዎች እየተስፋፉ ሲሆን ገበያዎቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ ስለመሆኑ ክትትል እየተደረገ ነው።
በተመሳሳይ በመዲናዋ የሚገኙ የሸማቾች ማህበራት ምርት ወደ ገበያ እንዲያስገቡ የከተማ አስተዳደሩ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡
ማህበራቱ ምርቶችን በትክክል ለህብረተሰቡ እንዲያደርሱም ነው ያሳሰቡት።
በአቋራጭ ለመክበር ጥረት በሚያደርጉ አካላት ላይ ደግሞ "ምህረት የለሽ" እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡
ኀብረተሰቡ የኑሮ ጫናውን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህ ወቅት በተለየ ሁኔታ በዘይትም ሆነ በሌሎች ሸቀጦች ላይ ዋጋ ሊያስጨምር የሚችል ምክንያት አለመኖሩንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።