የአድዋ ድል ከቀደምቶች የመሪነትን ሚና መማር እንደሚያስችል የአለም ተተኪ መሪዎች ሊገነዘቡት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል ከቀደምቶች የመሪነትን ሚና መማር እንደሚያስችል የአለም ተተኪ መሪዎች ሊገነዘቡት ይገባል
የካቲት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአድዋ ድል ከቀደምቶች የመሪነትን ሚና መማር የሚያስችል መሆኑን የአለም ተተኪ መሪዎች ሊገነዘቡት እንደሚገባ አምባሳደር ሙሌ ታረቀኝ አመለከቱ።
“ድህረ የኮሮና ወረርሽኝ ምርጥ መሪን መፍጠር” በሚል መሪ ቃል በቱርክ ኢስታንቡል በመካሄድ ላይ ባለው የተመድ ሲሙሌሽንስ ሞዴልስ ምርጥ ዲፕሎማት ኮንፍረንስ ላይ በቱርክ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሙሌ ታረቀኝ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል።
አምባሳደሩ ከተለያዩ ዓለም ሀገራት የተወጣጡ ወጣቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በተመድ አሰራርና እያጋጠው ያሉ ችግሮች፣ ኢትዮጵያ የተመድ እና አፍሪካ ህብረት መስራች መሆኗንና ለአፍሪካ ነፃነት ያደረገችውን አስተዋጽኦ አብራርተዋል።
በቅርቡም 126ኛው የአድዋ ድል በአል መከበሩን በማንሳት ወጣቶች ከቀደምት መሪዎች ትምህርት ወውሰድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በማከልም ከወጣቶች ስለሚጠበቀውና የዚህ አይነት መድረክ መዘጋጀቱና ተሳትፎ ማድረጉ የወደፊቱን መሪዎች ለመፍጠር አይነተኛ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
በመድረኩም 45 አገራትን የወከሉ ከ90 በላይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን 25 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተሳትፎ አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያኑ በተሳትፏቸው የተለያዩ ክርክሮች፣ ድርድሮች እና ባህላዊ ጭፈራዎችን በማቅረብ የሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ሲል በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል ።
ሞዴልስ ምርጥ ዲፕሎማት ኮንፍረንስ ግንዛቤ በማሳደግ የተሻለ ዲፕሎማት ለመፍጠር የሚሰራ ሲሆን ተመሳሳይ ፎረሞችን በአመት ሁለት ግዜ በቱርክ ያካሂዳል።