የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከተባበርን ከዚህ በላይ መሥራት እንደምንችል ማሳያ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከተባበርን ከዚህ በላይ መሥራት እንደምንችል ማሳያ ናቸው
የካቲት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)"በአዲስ አበባ ተጠናቀው ዛሬ የተመረቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከተባበርን ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ናቸው" ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች በ1.9 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 14 የመንገድ ፕሮጀክቶችን መርቀው ከፍተዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶች ከ13 እስከ 60 ሜትር የጎን ስፋትና ከ19 ኪ.ሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሲሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ናቸው ተብሏል።
ጎን ለጎንም ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው የእግረኛ መንገዶችና የመንገድ ዳር መብራቶችም ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከሃይሌ ጋርመንት-ጀሞ አደባባይ (አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መንገድ)፣ከራስ ደስታ -ቀጨኔ መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን- 8 ቁጥር ማዞሪያ፣ ከሽሮሜዳ ቁስቋም፣ ሲኤም ሲ ሚካኤል መሻገሪያ ድልድይ ከተመረቁ 14 ፕሮጀክቶች ውስጥ ይገኙበታል።
ፕሮጀክቶችን መርቀው የከፈቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን የመንገድ ትስስርና የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በራስ አቅምና በተያዘላቸው እቅድ መሰረት መጠናቀቃቸው"ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ማጠናቀቅ እንደምንችል ያሳየንበትም ነው" ብለዋል።
አገር በችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት የልማት ሥራዎች በታቀደላቸው መሰረት እንዲጠናቀቁ ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰው እነዚህ ፕሮጀክቶች የዚህ ውጤት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ዛሬ የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች "ከተባበርን ከዚህ በላይ መሥራት እንደምንችል ማሳያ ናቸው" ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
በቀጣይም በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ በመዲናዋ ትላልቅ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ተመርቀው ለኅዝቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አረጋግጠዋል።
ከተማዋን ተወዳዳሪ በማድረግ ብቁና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት እንዲሁም የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የመንገድ መረብ ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
የመንገድ ሽፋንን በማሳደግ ከፍተኛ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስረድተዋል።
የተመረቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች ባለሥልጣኑ በመዲናዋ አሁን ላይ እያስገነባቸው ከሚገኙ ከ100 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚያሳልጡና የመንገድ ደኅንነትን የሚያረጋግጡና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ ማሳለጫ ድልድዮችና የእግረኛ መንገዶችን እየገነባ መሆኑ ተገልጿል።