በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የቱሪዝም አቅሞችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የቱሪዝም አቅሞችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል
የካቲት 27/2014/ኢዜአ /በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የቱሪዝም አቅሞችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው በቱሪዝም ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ቅርሶችና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።
በሐረር ከተማ የሚገኙ የሐረሪ የባህል ማዕከል፣ የጀጎል ግንብ፣ የአርተር ራንቦ ማዕከል እና ሌሎች ታሪካዊ ሙዚየሞችን ተመልክተዋል።
በተጨማሪ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኘውን የሐርላ መንደር መካነ-ቅርስ እና የማህበረሰብ ሙዚየም እንዲሁም በአፋር ክልል የሚገኘውን የሃላይዴጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክን ጎብኝተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በጉብኝቱ የተሳተፉ ጋዜጠኞች፤ ኢትዮጵያ በርካታ አስደናቂ የታሪክ፣ ተፈጥሮና የባህል ሃብት ቢኖራትም በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ከቱሪዝም ልማት አኳያ ገና ያልተነኩ እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ በርካታ ጸጋዎች ያሉበት አካባቢ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
አካባቢው ካሉት የተፈጥሮ ጸጋዎች ባሻገር የበርካታ ታሪክና ስልጣኔ ባለቤት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ የቱሪዝም ሃብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት እና የቱሪዝም ጉዞ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የምስራቅ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የቱሪዝም መስመር ለመባል የሚችል፣ የተለያዩ የተፈጥሮ ጸጋዎች ፣ ባህል፣ ስልጣኔ የሚታይበት መሆኑን ገልፆ በዚህ መስመር የሐረሪን፣ የአርጎባን፣ የሶማሌን፣ የኦሮሞን ቀለም የሚታየበት መሆኑን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስኪያጅ አስናቀ ብርሃኑ በበኩሉ የቱሪዝም መስህቦችን ይበልጥ በማስተዋወቅ እና ስራ ላይ በማዋል ለዜጎች ሰፋፊ የስራ እድሎችን መፍጠር እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡
የዳይናሚክ ኢንተርቴይመንት አዘጋጅ አለምነሽ ኩምሳ በበኩሏ የመገናኛ ብዙሃን ስለ ሀገሪቱ የቱሪዝም ሃብት እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጻ የማስተዋወቅ ስራዎች ሲጠናከሩ የቱሪስት ፍሰቱ እንደሚሻሻል ተናግራለች፡፡
አካባቢዎቹን በሚፈለገው መልኩ ማልማት ከተቻለ ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፉ የቱሪዝም ገበያ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም ነው ያነሱት፡፡
በተጨማሪ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጠናከር እንዲሁም በዘርፉ ጥራት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥን ማጎልበት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ዜጎች አገራቸውን እንዲያዩ እና እንዲያውቁ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም አቅም ያላት አገር ብትሆንም ዘርፉ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገት ውስጥ ከ10 በመቶ ያነሰ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡