ቀጥታ፡

በመዲናዋ ከ3 ሺህ 600 ሄክታር በላይ ለሚሆኑ የፌደራል መንግሥት የመሬት ይዞታዎች ዲጂታል ካርታ እየተዘጋጀላቸው ነው

የካቲት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ ከ3 ሺህ 600 ሄክታር በላይ ለሚሆኑ የፌደራል መንግሥት የመሬት ይዞታዎች የዲጂታል ካርታ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን የፌዴራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በፌደራል መንግሥት ይዞታ ሥር ይገኛል ብለዋል።

እነዚህም የመሬት ይዞታዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሆኑን ገልጸው ፤ለአገሪቱ መስጠት የሚገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንዳይሰጡ መደረጉን ነው ያስረዱት።

በተለይም አንዳንድ ሰፋፊ የመንግሥት የመሬት ይዞታዎች ያለምንም ጥቅም ታጥረው፤አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች ማስወገጃ እስከመሆን መድረሳቸውን ለአብነት ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑም እነዚህንም ይዞታዎች ለሚፈለገው አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የይዞታዎቹን መረጃዎች የማጠናቀር ሥራ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይም በአዲስ አበባ ከ3 ሺህ 600 ሄክታር በላይ ለሚሆኑ የመንግሥት የመሬት ይዞታዎች የዲጂታል ካርታ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም ይዞታዎቹን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በመተባበር ወደ ኮርፖሬሽኑ የመሬት ባንክ የማዞር ሥራም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ እስከ 3 ሺህ 800 ሄክታር የመንግሥት የመሬት ይዞታ መኖሩን የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ገልጸው፤ ነገር ግን ይዞታዎቹ ከዚሀ አሃዝ እንደሚልቅ አስረድተዋል።

ለቀሪዎቹ ይዞታዎችም አስፈላጊውን መረጃ በማጠናቀር ዲጂታል ካርታ እንደሚዘጋጅላቸው በመጠቆም።

ኮርፖሬሽኑ የመሬት ልኬትና መረጃ አሰባሰብ ሥራውን ከጂኦ-ስፓሻል ኢንቲትዩት እንዲሁም መረጃዎቹን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ደግሞ ከመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጋር መሥራቱን ገልጸዋል።

በቀጣይ እነዚህ የተለዩትን ይዞታዎች በአግባቡ ለማልማትና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ከፍ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ አሰግንዝበዋል።

በተለይም ይዞታዎቹ ከማን ጋር መልማት እንዳለባቸው፣ እንዴት መልማት እንዳለባቸውና ምን አይነት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይዞታዎቹ ለቤት ልማት፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለአይ ሲ ቲ የአገልግሎት ዘርፍ ልማት እንዲውሉ ትኩረት መደረጉንና ለዚህም የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬት ይዞታ ምዝገባ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ወደ ሐረር፣ድሬዳዋና ሶማሌ ክልል ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በአምስት ዓመታት ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚገኙት ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የመንግሥት የመሬት ይዞታዎች ዲጂታል ካርታ ለማዘጋጀት እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም