ቀጥታ፡

ኢዜአ አንጋፋነቱን የሚመጥን የብዙኃን መገናኛ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የካቲት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አንጋፋነቱን የሚመጥን የብዙኃን መገናኛ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢዜአ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በማስመልከት ያዘጋጀውን አውደ ርዕይና የተቋሙን አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል፡፡

ኢዜአ ላለፉት 80 ዓመታት በዜና አገልግሎት ዘርፍ የኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮ በመሆን ዘመናትን የተሻገረ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉብኝታቸው ወቅት ኢዜአ የኢትዮጵያዊያንን የመረጃ ፍላጎት በማሟላት ለረጅም ዘመናት ያገለገለ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢዜአ ለበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አርአያ በሚሆን መልኩ ወጥና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

May be an image of 3 people and people standing

ኢዜአ ቀዳሚነቱን የሚመጥን ውብና ማራኪ ህንፃ በመገንባት ከተማችንን ተጨማሪ ውበት አጎናፅፏታል ያሉት ከንቲባዋ፤ ተቋሙ የተሰጠውን መሬት በትክክል በመጠቀም ለልማት ማዋሉንም ገልጸዋል፡፡

ለመዲናችን አዲስ አበባ ብሎም ለኢትዮጵያ ላለፉት 80 ዓመታት የሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢዜአ ጎን በመሆን ያግዛል፤ ያበረታታል፤ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ኢዜአ ለመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚመጥን ስራ እየሰራ በመሆኑ እጅግ ደስ ብሎናል፤ ለጥረቱ ሁሉ እናመሰግናለን ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ኢዜአ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ዘርፍ ለኢትዮጵያ የጎላ አበርክቶ ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

May be an image of 2 people and people standing

በኢዜአ የተሰነዱ የድምጽና ምስል መረጃዎች በኢትዮጵያ የተከናወኑ ሁነቶችን ወደ ኋላ ተመልሰን ለመዳሰስ የሚያስችሉ ትልቅ የታሪክ ማስረጃዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ኢዜአ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የከተማ መስተዳደሩ በቀጣይ ኢዜአ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ1934 ዓ.ም የተመሰረተና የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም