ፌዴራል ፖሊስ ለህዝብና መንግስት የሚሰጠውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለማሻሻልና የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ፖሊስ ለህዝብና መንግስት የሚሰጠውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለማሻሻልና የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለህዝብና መንግስት የሚሰጠውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለማሻሻልና የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በዋና መምሪያና በመምሪያ ደረጃ አዲስ ለተመደቡ የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
ስልጠናው በፖሊስ ዶክትሪንና በስነ-ምግባር፣ በተቋማዊ ለውጥና አመራርነት፣ በተቋሙ ስትራቴጂክ እቅድ፣ በወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎች እና በሰው ኃይል አስተዳደር ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደነበር ታውቋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ በመዋቅርና በአሰራር ሂደቶች ሲስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም ሰፊ ጥናት ተደርጎ አዲስ መዋቅር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በመዋቅሩም የፖሊስ አመራሩ ቀድሞ የነበረውን አስተሳሰብ በመቀየር መንግስትና ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ሰራዊቱን በአግባቡ መምራት የሚያስችል አቅም በመፍጠር ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አዲሱ መዋቅር አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በተለያዩ አገራት ልምድና ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲካተቱበት ተደርጎ መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት።
በተልዕኮ አፈጻጸም ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረምም ለኦፕሬሽን አመራሮች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይነት እስከ ታችኛው የአመራር እርከን ድረስ ስልጠናው እንደሚሰጥ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ለአመራሩ በየደረጃው የሚሰጠው ስልጠና መንግስትና ህዝብ በሚፈልገው ልክ የፖሊስ አገልግሎትን ለማሻሻል መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ለህዝብና መንግስት የሚሰጠውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለማሻሻልና የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሰጠው ስልጠና በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት ለመስራት፣ ለውጡን በባለቤትነት መንፈስ ይዞ ለማስቀጠልና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የፖሊስ አመራር ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ኮሚሽነር ደመላሽ ጠቁመዋል።
በአዲሱ መዋቅር ከተሰጠው ሥራና ኃላፊነት አንጻር የፖሊስን አገልግሎትና የመፈጸም አቅም ማሳደግና ሰራዊቱን በሚገባ ለመምራት የሚያስችል የአመራር ስልጠና ማግኘታቸውን አመራሮቹ ገልጸዋል።