ቀጥታ፡

በጎንደርና አካባቢዋ ያሉ እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጸጋዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል በሰላምና ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በጎንደርና አካባቢዋ ያሉ እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጸጋዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል በሰላምና ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት እንደሚገባ የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ፈንታ ተናገሩ።

በጎንደር የሰላምና የእድገት ማኅበር (ጎሰማ) እና በጎንደር መልሶ ማቋቋም ልማት ማኅበር (ጎልማ) ጥምረት የጎንደር ሰላምና ዕድገት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባኤውም የአማራ ልማት ማህበር ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ፈንታ፣ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው ጨምሮ ምሁራን፣ ተጋባዥና የጎንደር ተወላጅ እንግዶች ተሳትፈዋል።

"አብሮነት ለውስጥ ጥንካሬ፣ የውስጥ ጥንካሬ ለሰላም እና ልማት፣ ሰላምና ልማት ለሀገር ህልውና" በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ጉባኤ ጎንደር የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ፣ የአንድነት ተምሳሌት፣ የጀግኖች መፍለቂያና የቱባ ባሕል ባለቤት መሆኗ ተወስቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የጎንደርን ታሪካዊ መገለጫዎች የሚያደበዝዙና ታሪኳን የማይመጥኑ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ እና ሥርዓተ አልበኝነት እየተስተዋሉ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

ከጎንደር ጥንታዊ ታሪክና መገለጫ ጋር አብረው የማይሄዱ ድርጊቶችን በመቀልበስ ስምና ዝናዋን ከፍ በማድረግ ትንሣኤዋን ማብሰር እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።

የጎንደር ሰላም እና የእድገት ማኅበር (ጎሰማ) እና ጎንደር መልሶ ማቋቋም እና ልማት ማኅበር (ጎልማ) ለጎንደር ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ በመሥራት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

የአማራ ልማት ማህበር አልማ ሥራ አስፈጻሚና የጎንደር ሰላም እና የእድገት ማኅበር (ጎሰማ) የበላይ ጠባቂ አቶ መላኩ ፈንታ፤ የሰላም ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አለመሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ የሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሰረት የሰላም መረጋገጥ መሆኑን ተረድቶ በቅንጅት መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ የሰላም ጉዳይ የኔም ነው የሚለውን እንዲረዳም የሰላምን ዋነኛ ሥራው አድርጎ የተቋቋመው ጎንደር የሰላምና የእድገት ማኅበር (ጎሰማ) አበረታች ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሰላምን ማረጋገጥ ከተቻለም የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ በማልማት ከማህበረሰብ በተጨማሪ ለሀገርም ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን እንደሚቻል አንስተዋል።

የጎንደር ሰላም እና የእድገት ማኅበር (ጎሰማ) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ በላቸው፤ በጎንደር እና አካባቢው ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጸጋ በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በከተማዋ ወንጀልን በጋራ በመከላከልና ሰላምና ጸጥታዋን በማስጠበቅ የጎንደርን ገጽታ በመገንባት የቱሪዝም መናገሻነቷን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በጎንደርና አካባቢዋ ያሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመጠቀም ወጣቶችን የሥራ ባለቤት በማድረግ ከሱስ ጥገኝነት ማላቀቅና ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚጠይቅም በጉባኤው አጽንኦት ተሰጥቷል።

በሰላም፣ በደህንነት፣ በልማት፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ላይ ሲያከናውኑት የቆዩትን ተግባር በማስቀጠል የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩም ማህበራቱ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም