የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ልማት ቅንጅት ፈጥረው ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ልማት ቅንጅት ፈጥረው ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ልማት ቅንጅት ፈጥረው ሊሰሩ እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ እየሱስወርቅ ዛፉ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የባንኮች ዘርፍ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም የፋይናንስ ተቋማት ሊገጥሟቸው የሚችሉትን ተግዳሮቶች ለመቋቋም የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።
የምጣኔ ሃብት ምሁሩ እየሱስወርቅ ዛፉ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ዓለም አሁን ላይ ዘርፉ በቴክኖሎጂ፣ በገበያ፣ በፋይናንስና ሌሎችም መስኮች በእጅጉ እየተቆራኘ መጥቷል።
በመሆኑም ለዘመናት ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ተደርጎ የቆየው የኢትዮጵያ የባንክ ሴክተር ክፍት የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ይናገራሉ።
በመሆኑም ዘርፉ ለውጭ ባለሃብት ክፍት ሲደረግ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ባንኮችና ሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት በቴክኖሎጅና በሰው ሃይል ልማት ላይ በቅንጅትና በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጠንካራ የሚባሉ የፋይናስ ተቋማት ቢኖሩም በአለም አቀፍ ደረጃ ሲመዘኑ ግን ገና ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።
በመሆኑም አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በተቀናጀ መልኩ ለመስራት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
የባንኮች ሴክተር አለም አቀፍ ውድድሩን ተቋቁሞ ለመዝለቅ ከቴክኖሎጂና የበቃ የሰው ሃይል በተጨማሪ የአሰራርና ሌሎች ሲስተሞችንም መቃኘት ይጠይቃል ሲሉ አብራርተዋል።
የባንኩን ዘርፍ መንግስት ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ ያለውን እሳቤ ያደነቁት አቶ እየሱስወርቅ፤ ሁኔታውን በመከታተል መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።