ቀጥታ፡

ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ይደግፋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።

ኢዜአ ከሁነቶች ዘገባ ያለፈ ጠንካራ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የሚዳስሱ ስራዎችን ማከናወን እንዳለበትም አገልግሎቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን 80 ዓመታት ጉዞ የሚዘክር አውደ-ርዕይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የተከፈተ ሲሆን፤ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት፤ ኢዜአ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቋም ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ለነበሩ አፍሪካውያን ድምፅ ነበር።

ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ሕዝባዊ የዕለት ተለት እንቅስቃሴዎችንና እያንዳንዱን ታላላቅ ሀገራዊ ሁነት በመዘገብ አበርክቶው ጉልህ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በእያንዳንዱ አገራዊ የታሪክ ሂደት ውስጥ ኢዜአ አሻራውን ያሳረፈ ትልቅ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ የእስካሁን ጉዞው በታሪክ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም ትልቅ አገራዊ ኃላፊነቶች ስለሚጠብቁት በቴክኖሎጂ ራሱን ለማዘመን እያደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ብቁ ባለሙያዎችን በመገንባት ተልዕኮውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ሕዝብ፣ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ባለቤት በመሆኗ ኢዜአ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በዓለም ጠንካራ መሰረት ካላቸው የዜና ተቋማት ጋር በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የዘገባ ጥራት ላይ ማተኮር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ኢዜአ ከሁነቶች ዘገባ ባለፈ ጠንካራ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ተንትኖ ሊሰራ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ለሚያደርገው ጥረት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም