የካራማራ ድል ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ ልጆቿ በጀግንነት ደማቅ ታሪክ የፃፉበት ልዩ ታሪካዊ ክስተት ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የካራማራ ድል ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ ልጆቿ በጀግንነት ደማቅ ታሪክ የፃፉበት ልዩ ታሪካዊ ክስተት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ወራሪን ያሸነፈችበት 44ኛው የካራማራ ድል በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የድሉ መታሰቢያ ሐውልት በድምቀት ተከብሯል፡፡

በወቅቱ በሶማሊያ መሪ የነበረው ጄነራል መሀመድ ሲያድ ባሬ "ታላቋን ሶማሊያ መፍጠር" በሚል የተሳሳተ እሳቤ የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት ጥሶ በመግባት ወረራ በፈፀመበት አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት መክተው ከምድራቸው አስወጡ።

በኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት ድሉ ሲጠናቀቅ የመጨረሻው ውጊያ የነበረው ካራማራ ላይ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የዚሁ ድል 44ኛ አመት መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል፡፡

የአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝም እና ኪነ ጥባባት ምክትል ቢሮ ሃላፊ አርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሃት፤ የካራማራ ድል ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ ልጆቿ በጀግንነት ደማቅ ታሪክ የሰሩበት ልዩ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ድልም ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ሉዓላዊነት ማጽናት መቻላቸውን ጠቅሰው በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጎን ለቆሙት የኩባ ህዝብና መንግስትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የካራማራ የድል በዓል ታላቅ የቱሪዝም መስህብ መሆን የሚችል የታሪክ አካል በመሆኑ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆን ባለፈ ለሁለቱ አገሮች ወዳጅነት መጠናከር የማይደበዝዝ አሻራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ጆርጅ ሊፍብሬ ኒኮላስ፤ ኩባና ኢትዮጵያ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ በወቅቱ የሶማሊያ መሪ በተወረረችበት ወቅት ኩባ የቁርጥ ቀን አጋሯ እንደነበረች አስታውሰው አሁንም አብሮነትና ትብብራቸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተለይም የጤናው ዘርፍ እንዲጠናከር ኩባ ከፍተኛ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን ጠቅሰው ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል።

የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ማህበር ፕሬዚዳንት ሺበሺ ካሣ፤ ኩባ ኢትዮጵያን በመደገፍ በተለይም በትምህርት ዘርፍ ያደረገችው እገዛ ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኑኘት ተወክለው የተገኙት ሻምበል ባሻ ፍቅሩ ከበረ፤ ''ኢትዮጵያዊነት በልብ እስካለ ድረስ ሁሉንም ጉዳይ በድል መወጣት እንደሚቻል ካራማራ ምስክር ነው'' ብለዋል፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ለአገር ህልውና መከበር የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ዘንድሮ ለ44ኛ ጊዜ የተከበረው የካራማራ ድል በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የቀድሞ የሰራዊት አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም