ኢትዮጵያ የገጠሟትን መልከ ብዙ ፈተናዎች በአሸናፊነት እንድትወጣ ከመንግስት ባለፈ የሁሉም አካላት ጥረት ሊታከልበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የገጠሟትን መልከ ብዙ ፈተናዎች በአሸናፊነት እንድትወጣ ከመንግስት ባለፈ የሁሉም አካላት ጥረት ሊታከልበት ይገባል
አዲስ አበባ የካቲት 26/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠሟትን መልከ ብዙ ፈተናዎች በአሸናፊነት እንድትወጣ ከመንግስት ባለፈ የሁሉም አካላት ጥረት ሊታከልበት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ/ኢሕአፓ ጠየቀ።
ፓርቲው በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ግማሽ ሚሊን ብር ግምት ያለው የእንስሳት መኖ ድጋፍ አድርጓል።
የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቦ የኢሕአፓ ተግባር የኢትዮጵያ የመጠላላት የፖለቲካ መልክ እየተሻሻለ መምጣቱን በተግባር አሳይቷል ብሏል።
የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ መጋቢ ብሉይ አብርሐም ሃይማኖት፤ ጅግጅጋ ከተማ ተገኝተው ለሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጸህፈት ቤት ሃላፊ መሃመድ ሻሌ ድጋፉን አስረክበዋል።
የሶማሌ ክልል ለኢሕአፓ የትግል መሰረት እንደነበር ያስታወሱት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው ኢሕአፓ ከአባላቱ አሰባስቦ የተቻለውን ድጋፍ ለማድረግ እንደወሰነ ገልጸዋል።
በዚህም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ከግማሸ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የእንስሳት መኖ ማስረከቡን ገለፀው፤ በቀጣይም ሌሎች ድጋፎችን እናደርጋለን ብለዋል።
በተመሳሳይ ፓርቲው በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ለተጎዱ ወገኖች ድጋፈ ለማድረግም ተጨማሪ ሀብት በውስጥና በውጭ አገራት ከሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎች እያሰባሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።
የገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ ጥምረቱ ደጋፊዎቹን በማስተባበር ለሌላ ድጋፍ እንደተዘጋጀ አረጋገጠዋል።
ኢትዮጵያ በድርቅ፣ በግጭትና በጦርነት የተፈተነችበት ወቅት መሆኑን ተከትሎ ለችግር የተዳረገውን ህዝብ ከችግር መታደግ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም አካላት ሃላፊነት መሆን አለበት ብለዋለ።
የሚደረጉ ድጋፎችም ከተናጠል ይልቅ በመንግስት የሚመራ ከሁሉም አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ነጻና ገለልተኛ ተቋም ተቋቁሞ ቢሰራ የበለጠ ድጋፍ አሰባስቦ ተጎጂውን ህዝብ መታደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የሱማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መሃመድ ሻሌ፤ ኢሕአፓ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ብዙ ጊዜ ፓርቲዎች ከጥላቻ ወጥተው በጋራ የመስራት ልምድ እንዳልነበራቸው ጠቅሰው አሁን ላይ ግን በተለይም ለህዝብ እና ለአገር ህልውና በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ብልጽግናም እንደ ገዥ ፓርቲነቱ ይህ አይነት ተሞክሮ እንዲጣናከር በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ 22 ፓርቲዎች ጥምረት በድርቅ ለተጎዳው የሶማሌ ክልል ህዝብ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸው ኢሕአፓ መሪነቱን ወስዶ ድጋፉን ቀድሞ በማድረሱም አመስግነዋል።
በሶማሌ ክልል ካሉት 11 ዞኖች በ10ሩ ባለፉት 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልፀው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ እያቋረጡ ወደ ከተማ መግባታቸውን አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት ከራሱ በጀት በተጨማሪ ከፌዴራልና ከክልል መንግስታት የተገኙ ድጋፎችን በማሰባሰብ ድርቁ ሊያደርሰው የሚችልውን ጉዳት መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።
እስካሁንም በቁም እንስሳት ላይ ከደረሰው እልቂት በስተቀር የሰው ህይወት እንዳይጠፋ መከላከል መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይም ድጋፉን ለማጠናከር የክልሉ ካቤኔ ተጨማሪ በጀት እንዲኖር መወሰኑን አንስተዋል።
ከዚህ ወር በኋላ ባለው ወቅት ዝናብ እንደሚጠበቅ ገልጸው በክልሉ ድርቁ ያስከተለውን ቀውስ ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።