ቀጥታ፡

ኢዜአ የመረጃ ተደራሽነቱን በማስፋትና የቴክኖሎጂ አቅሙን ይበልጥ በማሳደግ የመላ አፍሪካ ድምፅ ለመሆን መስራት አለበት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የመረጃ ተደራሽነቱን በማስፋትና የቴክኖሎጂ አቅሙን ይበልጥ በማሳደግ የመላ አፍሪካ ድምፅ ለመሆን በትኩረት መስራት እንዳለበት የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ገለጹ።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰጠኝ አቡሃይ፤ ኢዜአ ከተጋረጠበት የመፍረስ አደጋ ወጥቶ በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን አድንቀዋል።

አሚኮ መረጃ ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ ከኢዜአ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ኢዜአ ሌላኛው ተቋማችን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይም አሚኮ በተለያዩ ክልሎች ሽፋኑን የማስፋት እቅድ ያለው በመሆኑ ለስኬቱ ከኢዜአ ጋር የሚኖረውን ትብብር ያጠናክራል ብለዋል።

ኢዜአ አሁን ያለውን የመረጃ ተደራሽነት ማጠናከር በተለይም ተዓማኒነትና ፈጣን መረጃ ለማድረስ ይበልጥ እንዲሰራ የጠየቁት ደግሞ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነቢዩ ጥዑመልሳን ናቸው።

ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ትላልቅ ጉዳዮችን ሽፋን በመስጠት ለንግድ የመገናኛ ብዙሃን መረጃ ተደራሽ ለማድረግ መስራት አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ዋና ሥራ አስኪያጅ ዝናቡ አስራት፤ የኢትየጵያ መገናኛ ብዙሃን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቅንጅት በመስራት ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ኢዜአ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ተደራሽ በማድረግ ትልቁን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ኦቢኤን በቀጣይ ከኢዜአ ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ አገራችንን ለማቃናት በሚደረገው ርብርብ ብዙ ሆነን እንደ አንድ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) የዜና ክፍል ኃላፊ ጋዜጠኛ ጌራ ጌታቸው፤ ኢዜአ የመንግስትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለህዝብ የማድረስ ግዴታ እንዳለበት ሁሉ የህዝቡን እሳቤ ለመንግስት ለማድረስም በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል ብሏል።  

የመገናኛ ብዙሃኑ አመራሮች አክለውም ኢዜአ ከኢትዮጵያ ባሻገር አፍሪካዊ ጉዳዮችን ሽፋን በመስጠትም መልካም ተሞክሮ እንዳለው አንስተዋል።

በተለይም በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢዜአ በርካታ መረጃዎችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ በማድረግ የተሳካ ስራ ማከናወኑን አስታውሰዋል።

የኢዜአ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ስራ ማከናወን ለሌሎች የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ጥንካሬ እንደሚሆንም ሃላፊዎቹ ጠቅሰዋል።

አፍሪካዊ ትብብር እንዲጠናከር ሁሉም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በጋራና በትብብር መስራት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

በመሆኑም ኢዜአ የመረጃ ተደራሽነቱን በማስፋትና የቴክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ የመላ አፍሪካ ድምፅ ለመሆን በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው ኢዜአ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙኃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም