በአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ ጉዞ ከ264 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ ጉዞ ከ264 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ተሰበሰበ
የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ ጉዞ ከ264 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ከዳያስፖራው መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት መምጣታቸው የሚታወስ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው የመጡ ዳያስፖራዎች በቆይታቸው 264 ሚሊዮን 526 ሺህ 108 ብር ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የዳያስፖራው አባላት 114 ሚሊዮን 189 ሺህ 780 ብር የሚያወጣ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማድረጋቸውን ገልጿል።
ዳያስፖራው 98 ሚሊዮን 805 ሺህ 768 ብር የሚገመት መድሐኒትና የህክምና ግብአቶች ወደ አገር ቤት ይዞ በመምጣት ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል።
የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት 49 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ከዳያስፖራው ማሰባሰብ መቻሉን ገልጿል።
ዳያስፖራው ለበጎ አድራጎት ስራዎች 1 ሚሊዮን 930 ሺህ 560 ብር ድጋፍ ማድረጉን ነው ኤጀንሲው የገለጸው።
በተጨማሪም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ‘አንድ ሻንጣ ለወገኔ’ በሚል መሪ ሀሳብ ለተቸገሩ ወገኖች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ዳያስፖራዎች አልባሳትን ለማሰባሳብ በተደረገው እንቅስቃሴ ከታህሳስ 21 ቀን እስከ ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም 9 ሺህ 198 የተለያዩ አልባሳቶችን ማሰባሰብ መቻሉን አመልክቷል።
በአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ በአገርና ክልል አቀፍ ደረጃ 55 ኩነቶች(ኤቨንትስ) መዘጋጀታቸው ተጠቅሷል።
በዳያስፖራው ጥሪ ፖለቲካዊ፣ዲፕሎማሲያዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራው ኤጀንሲ ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ