44ኛው የካራማራ የድል በዓል በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
44ኛው የካራማራ የድል በዓል በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ተከበረ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) 44ኛው የካራማራ የድል በዓል በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ።
በወቅቱ በሶማሊያ የነበረው ጄነራል መሀመድ ሲያድ ባሬ "ታላቋን ሶማሊያ መፍጠር በሚል የተሳሳተ እሳቤ" የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት ጥሶ በመግባት ወረራ በፈፀመበት አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያን በጀግንንት መክተው ከምድራቸው አስወጡ።
በኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት ድሉ ሲጠናቀቅ የመጨረሻው ውጊያ የነበረው ካራማራ ላይ እንደነበር ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት መንግስቱ ኃይለማሪያም ወረራውን ተከትሎ የእናት ሀገር ጥሪ ሲያቀርቡ ኢትዮጵያዊያን ከዳር ዳር ተነሱ።
በዚህም ሚሊሻዎች፣ መደበኛው ጦርና በኩባ መንግስት ድጋፍ የተገኙ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ወታደሮች ድጋፍ ታክሎበት በካራማራ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን አሸነፉ።
እለቱን በማስመልከትም በኢትዮጵያ ለ44ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ለመታሰቢያነት በቆመው ሃውልት ዙሪያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
የበዓሉ መከበርም ለአገራዊ አንድነት ትልቅ ፋይዳ እና ትርጉም ያለው መሆኑ በመርሃ ግብሩ ላይ ተነግሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ የቀድሞ የሠራዊት አባላት፣ በኢትዮጵያ የኩባ ሪፕብሊክ አምባሳደርና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኦጋዴን ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው በኢትዮጵያና በሶማሊያ ወራሪ ሃይል መካከል የተደረገው ጦርነት የዛሬ 44 ዓመት ነበር።