ቀጥታ፡

የሰነድ ማሻሻያዎችን በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጁ ነን--ፓርቲዎች

የካቲት 26/2014 (ኢዜአ) የሰነድ ማሻሻያዎችን በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለ26 አገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ማስታወቁ ይታወሳል።

ከፓርቲዎች መካከል ብልጽግና ፓርቲ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓም ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄዳል።

የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ፤ከምርጫ ቦርድ በቀረበው ጥያቄ መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ በቅድመ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

አቶ ግርማ በቀለ ወ/ዮሃንስ የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እንደገለፁት ቀደም ሲል የነበረው ሰነድ ምርጫ ቦርድ አዲስ ካወጣው አዋጅ ጋር አብሮ የሚሄድ ባለመሆኑ የተለያዩ አንቀፆች ማሻሻያ ማድረግ የግድ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ፓርቲው በተሰጠው የግዜ ገደብ ውስጥ ቅድመ ጉባኤ ምክክር በሶስት ማእከሎች ለማድረግ ታስቧል ብለዋል፡፡

ሀዋሳ፣ አዲስ አበባ እና ባህርዳር በሚቀጥሉት ቅዳሜና እሁድ ለማድረግ በእቅድ መያዙም ገልጸዋል፡፡

የቅድመ ጉባኤ ምክክሩ ከተካሄደ በኋላ አስፈላጊ የሆኑ የሰነድ ማሻሻያዎች በማድረግ እና ጠቅላላ ጉባኤው በማከናወን ለምርጫ ቦርድ ለማስገባት መታሰቡ ገልፀዋል።

የለውጥ ጊዜውን ተከትሎ 5 የተለያዩ ፓርቲዎች በመዋሃድ የተፈጠረ ፓርቲ መሆኑ የገለፁት ሊቀመንበሩ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረጉ የቆዩ የድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደርያ ደንብ እንደሚታይም ጠቅሰዋል፡፡

ፓርቲያችን ፍፁም ሰላም የህግ የበላይነት የሰፈነባት አገር ሰላማዊና መረጋጋት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ማየት የምንፈልግ እንደመሆናችን ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን ብለዋል፡፡

በመድረኩ የድርጅቱ የአሰራር ስርዓት እንዴት መጠናከር እንዳለበት በመነጋገር እና ቀጣይ አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት የሚሉ ጉዳዮች ይነሳሉ ብለዋል አቶ ግርማ፡፡

ፓርቲው ቀደም ብሎ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሰነዶች በማሻሻሉ በጠቅላላ ጉባኤ አስፀድቆ ለምርጫ ቦርድ እንደሚያስገባ አቶ አለሙ ኮይራ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ገልፀውልናል፡፡

ዋና ፀሃፊው ጨምረውም አገራዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ከተስተካከሉ መጋቢት 07/2014 ዓ/ም ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ መታሰቡ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው ያለፈው ቃለ-ጉባኤ በማስፀደቅ የፓርቲው የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በማድመጥ ለቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዋና ጸሀፊው ገልጸዋል።

በመድረኩም ቀደም ሲል የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤ በማድመጥ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት እንደሚደረግ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም