ዳያስፖራዎች በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

62

የካቲት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኖርዌይና አሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

'እንቁም ለኢትዮጵያ በኖርዌይ' የተሰኘው ድርጅት 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር፤ በሆስተን ቴክሳስ አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ደግሞ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ነው ድጋፉ ያደረጉት።

ድጋፉን ለኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር አይደሩስ ሃሰን አስረክበዋል።

ድጋፉን በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው የአፋርና የአማራ ክልሎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ያደረጉት መሆኑን ጠቁመዋል።

እንቁም ለኢትዮጵያ በኖርዌይ ተወካይ ዶክተር ኃይሉ ከበደ፤ ድጋፉ በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች መልሶ ለማቋቋም ይውላል ብለዋል።

በቀጣይም በችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማቋቋም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በሆስተን ቴክሳስ አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ተወካይ አቶ ፍሬው መኮንን በበኩላቸው ድጋፉ ለጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ማቋቋሚያነት እንደሚውል ገልጸዋል።   

በቀጣይም በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትን በማስተባበር የሚያደጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነር አይደሩስ ሃሰን በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።  

ኢትዮጵያዊያኖች በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን  በጋራ በመሆን መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም