"ፈርስት ሂጅራ" የተሰኘ አለም አቀፍ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ይካሄዳል

111

አዲስ አበባ የካቲት 25/2014 /ኢዜአ/ "ፈርስት ሂጅራ" የተሰኘ አለም አቀፍ ፌስቲቫል በመጪው ሚያዚያ ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ሊካሄድ ነው።
ፌስቲቫሉ በዳራ ሚዲያና ኤቨንት ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

ፌስቲቫሉ የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ ኤክስፖ መርሃ ግብሮችን ያካተተ መሆኑም ተጠቅሷል።

የዳራ ሚዲያና ኤቨንት ሥራ አስኪያጅ አቶ አቡድልፈታህ ሱሌይማን ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ፌስቲቫሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አሕመድ ለዘንድሮ የረመዳን ወር በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ  ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ፌስቲቫሉ ከሚያዚያ 19 እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በፌስቲቫል ከተለያዩ የዓለም ዳርቻ የሚመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በመጭው ግንቦት 6 እና 7/2014 ዓ.ም ዝክረ ነጃሺ ሽልማት፣ ቴያትር  እንዲሁም "ፈርስት ሂጅራ" የተሰኘ  የሩጫና የእርምጃ  ውድድር መሰናዳቱንም ጠቁመዋል።

በፌስቲቫሉ ለማረሚያ ቤቶች የሚሆን የመጻህፍት ልገሳና የደም ልገሳ መርሃ ግብሮች ያካተተ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም