የአምራች ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል
አዲስ አበባ የካቲት 25/2014(ኢዜአ) የአምራች ኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የአምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ አዘጋጅነት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሁለት ቀናት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመሥጠት ላይ ይገኛል።
ሥልጠናው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማጎልበት በዘርፉ የሚስተዋሉ የአቅም ክፍተቶችን ለመፍታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እድገት ቀጣይነት መረጋገጥ አለበት።
ለዚህም ደግሞ የዘርፉን ተዋናዮች ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ድጋፎች መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመው በዚህም ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 11 ንኡስ ዘርፎች መኖራቸውንና የእያንዳንዳቸው ዘርፎች የሚገጥማቸውን ችግሮች በመለየት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ድጋፎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሥልጠናዎቹ የምርት አቅሞችን ማዳበር፣ የምርታማ አቅምን በማጎልበት በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የፖሊሲ አማራጮችና ስትራቴጂዎችን ለማሳየት ያለመ ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም የአገር ውስጥና የግሉ ንግድ ምርታማነት መዋቅራዊ በማድረግ የኢኮኖሚ ሽግግርን በማጎልበት ረገድ ያላቸውን ሚና ማሳደግም የሥልጠናው ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም አዲሱ የኢንዱስትሪና መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን በተሻለ ሁኔታ ለመተግበር እንደሚረዳም ነው ያስረዱት።
የመንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ የአቅም ግንባታና ዘላቂ ልማት ቢሮ የኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ አድገትን በአቅም ግንባታ እንደሚደግፍ አረጋግጧል።