ቀጥታ፡

የልማት ሥራዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመደገፍ የቁጠባ ባህልን ማሳደግ ይገባል

የካቲት 25 2014 (ኢዜአ) በአገሪቱ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመደገፍ የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል መጎልበት እንደሚገባው  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10ኛ ዙር ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሐግብር እጣ ወጥቷል።

የቁጠባ መርሐግብሩ ሁለት የመኖሪያ አፓርትመንቶች፣ 10 ዘመናዊ አውቶሞቢሎች፣ 30 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችና 30 ላፕቶፖች አካቷል።

ባንኩ በይቆጥቡ ይሸለሙ የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን በማረም መርሐግብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ ላለፉት 80 ዓመታት የኅብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማዳበር የሚያስችሉ የተለያዩ የማበረታቻ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ባንኩ ባለፉት 10 ዓመታት ዜጎች ቁጠባ እንዲጀምሩ የሚያበረታታ በሽልማት የተደገፈ የቁጠባ መርሃ ግብር በስፋት እንደሰራበት ጠቅሰዋል።

ይህም የአገሪቱን የልማት ጉዞ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመደገፍና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል 'ሀብት ማሰባሰብ' ስለሚያስፈልግ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።  

የአገሪቱን የልማት ተግባራት በዘላቂነት ለመደገፍ ከፍተኛ ኃብት ማሰባሰብ ይጠይቃል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ የቁጠባ ባህሉን ሊያጎለብት ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

"ቁጠባ እንደ አገርም ሆነ እንደ ግለሰብ ትልቅ ፋይዳ ያለው የብልሆች ምርጫ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም