ኢዜአ በአፍሪካ ተመራጭ የዜና ወኪል ለመሆን መትጋት ይኖርበታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በአፍሪካ ተመራጭ የዜና ወኪል ለመሆን መትጋት ይኖርበታል
አዲስ አበባ የካቲት 25/2014(ኢዜአ) ኢዜአ በአፍሪካ ተደራሽ፣ ተመራጭና ተዓማኒ የዜና ወኪል ለመሆን መትጋት ይኖርበታል ሲሉ የቀድሞ የኢዜአ ባልደረቦች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የ80 ዓመት ጉዞ እንዲሁም የአገር ሕልውናን በማስጠበቅ ረገድ ያበረከተውን ሚና የሚቃኝ የፓናል ውይይትና አውደ ርዕይ ዛሬ ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ የመከላከያ ሚኒስትርና የኢዜአ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢዜአ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የተቀቋሙ የቀድሞ አንጋፋ የሥራ ባልደረቦች መካከል አቶ ተክሌ ተስፋልደት ፣ አቶ ሰብስቤ ከበደእና አቶ ደበበ ቡርቃ እንደገለጹት፤ ኢዜአ ላለፉት በርካታ ዓመታት የአገሪቱ ዋነኛ የዜና ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ አንጋፋ ተቋም ነው።
ተቋሙ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ግንባታ የሚያበረታታ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው የሚሰራውን ዜናና ዜና ነክ ሥራዎች በፍጥነትና በጥራት ለዝህብ ለማድረስ ያስችለዋል ብለዋል።
ይህም ተቋሙ ከዚህ ቀደም የነበሩበትን ፈተናዎች አልፎ ወደ ከፍታ እያቀና መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ካለፉት ጊዜያቶች በተሻለ መልኩ ትልቅ እድገት ያሳየ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በኋላም በዜና አቅርቦት የተጠናከረ ሥራ መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ተቋሙ የብዙ ዓመት ልምዱንና የሰው ኃይሉን ተጠቅሞ ትክክለኛ፣ እውነተኛና ጥራቱን የጠበቀ ተዓማኒነት ያለው መረጃን በፍጥነት በማድረስ ከፍ ብሎ መታየት ይኖርበታልም ነው ያሉት።
ተቋሙ አገር ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች የሚዲያ ተቋማት በተሻለ መልኩ ተደራሽነቱ የሰፋ እንደመሆኑ ያለውን ሰፊ እድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማጠናከርም ሕዝቦችን ይበልጥ በሚያቀራርቡና የአገሪቱንም እድገት በሚያፋጥኑ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ተቋሙ አደረጃጀቱን ከዚህ በበለጠ መልኩ በማጠናከር በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ተደራሽና ተመራጭ የዜና ወኪል ለመሆን መትጋት ይኖርበታልም ነው ያሉት።
በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው ኢዜአ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙኃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ኢዜአ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን “በአዲስ ምዕራፍ-አስተማማኝ የዜና ምንጭ” በሚል መሪ ኃሳብ እያከበረ ነው።