በተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በ14 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደረሰ

84

ነገሌ የካቲት 25/2014/ኢዜአ/--- በጉጂ ዞን ጎሮዶላ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና በ14 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወረዳው ፖሊስ ወንጀል መከላከል ሹም ኢንስፔክተር አለማየሁ ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ላይ ከነገሌ ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቢታታ ቀበሌ ነው።

ከነገሌ 45 ሰው አሳፍሮ ወደ ሻሸመኔ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ  ኮድ 3- 47422 ኦሮ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመገልበጡ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።

በአደጋው የአንድ ሰው ህይወት ወድያው ሲያልፍ በ14 ሰዎች ላይ  ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የነገሌ አጠቃላይ ሆስፒታል ማዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መስፍን ሆርዶፋ በአደጋው አንድ ሰው ከባድና 13 ሰዎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው  መሆኑን ጠቁመው ተጎጂዎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም