የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር መጋቢት 04 ይፈጸማል

63

የካቲት 25/2014/ኢዜአ/ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሥርዓተ ቀብር እሁድ መጋቢት 04 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚፈጸም ተገለጸ።

የቤተክርስትያኗ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዕረፍት ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ስርዓተ ቀብራቸውን በተመለከተ ተወያይቷል።

በዚህም መሠረት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሥርዓተ ቀብር መጋቢት 04 ቀን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በ1980 ዓ.ም ነሐሴ 29 ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ተብለው የተሾሙ ሲሆን ላለፉት 34 አመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቤተክርስቲያኗ ትምህርት የሆኑትን አቋቋም፣ ድጓና ዝማሬ መዋስዕት በላቀ ሁኔታ የተማሩ መሆናቸውን ከሕይወት ታሪካቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም