ቀጥታ፡

የኢዜአ የ80 ዓመት ጉዞ እና የአገር ሕልውናን በማስጠበቅ ረገድ ያበረከተውን ሚና የሚቃኝ የፓናል ውይይትና አውደ-ርዕይ ይካሄዳል

የካቲት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የ80 ዓመት ጉዞ እንዲሁም የአገር ሕልውናን በማስጠበቅ ረገድ ያበረከተውን ሚና የሚቃኝ የፓናል ውይይትና አውደ-ርዕይ ዛሬ ይካሄዳል።

ኢዜአ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን “በአዲስ ምዕራፍ-አስተማማኝ የዜና ምንጭ” በሚል መሪ ቃል እያከበረ ይገኛል።

የበዓሉ አካል የሆነው የኢዜአ የ80 ዓመት ጉዞ እንዲሁም የአገር ሕልውናን በማስጠበቅ ረገድ ያበረከተውን ሚና የሚቃኝ የፓናል ውይይትና አውደ-ርዕይ ዛሬ በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ይካሄዳል።

በፓናል ውይይቱ ላይ “የዜና አገልግሎቶች ምንነት፣ ባህሪይና ሚና” በሚል ርዕስ ኢዜአ ከአመሰራረቱ አንስቶ ያለፈበትን ሂደትና ያበረከተውን አስተዋጽኦ እንዲሁም ድርጅቱ በቀጣይ ምን ለመስራት እንዳቀደ የሚያመላክቱ ጉዳዮች የያዘ ጽሁፍ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ኢዜአ ከለውጡ በኋላ የጸጥታ ጉዳዮች፣ የሕልውና ዘመቻና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጨምሮ ሌሎች አበይት ጉዳዮች ላይ የሰራቸውን ዘገባዎችና የነበረውን ሚና የተመለከተ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል።

ከፓናል ውይይቱ በተጨማሪ የኢዜአ የ80 ዓመት ጉዞን የሚያሳይ አውደ-ርዕይም ይካሄዳል።

ኢዜአ ከምስረታው ጀምሮ እስከአሁን ድረስ መረጃዎችን ተደራሽ ያደረገባችውን ስራዎች የሚያሳዩ ፎቶዎች ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን፤ ፎቶዎቹ ኢዜአ የሕልውናው ማስከበር ዘመቻን ጨምሮ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።

ኢዜአ ለዜናና ዜና ነክ ስራዎች ሲጠቀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች በአውደ-ርዕዩ ላይ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተዘጋጀው የፓናል ውይይትና አውደ-ርዕይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች፣ የኢዜአ ባለድርሻ አካላት፣ የቀድሞ የድርጅቱ ሰራተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢዜአ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት ባዘጋጀው መርሃ ግብር ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስና ሌሎች ስራዎችን ለባለድርሻ አካላት የካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም ማስጎብኘቱ ይታወሳል።

በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው ኢዜአ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

ተቋሙ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም