ኤጀንሲው የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረገ
የካቲት 24/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረገ፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮምና የአዲስ አበባ ትራፊክ ማንጅመንት ኤጀንሲ የትራፊክ ቅጣትን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ ተቋማቱ ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመሆን ጉዳዩን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በአሰራሩ መሰረት የትራፊክ ደንብ ቅጣት ክፍያን 6050 አጭር ቁጥርን በመጠቀም መፈጸም ይቻላል ነው የተባለው፡፡
አሽከርካሪዎች በቴሌብር አማካኝነት ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ በማስቻል ቀልጣፋ አግልግሎትን ተደራሽ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ አሰራሩ ለትራፊክ ቅጣት ክፍያ የሚባክን ጊዜን ለመቀነስ ያግዛል፡፡
የወረቀት አሰራርን በማስቀረት ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ይህም እንደ አገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የቴሌ-ብር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም በቅርቡ የኢትዮጰያ አየር መንገድ ትኬት ግዥን እና ወርሃዊ የውሃ ፍጆታ አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር መፈጸም የሚቻልበትን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማእከል ዳይሬክተር ኢንጂነር ትዝታ ገብረማሪያም በበኩላቸው፤
አሽከርካሪዎች በአገልግሎቱ አሰጣጥ ቅልጥፍና ላይ ቅሬታ ሲያነሱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ አዲሱ አሰራር በዘርፉ የሚነሳውን ቅሬታ በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አሰራሩ አሽከርካሪዎች በወረፋ ምክንያት የሚያባክኑትን አላስፈላጊ ጊዜና ገንዘብ እንደሚያስቀር የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የቀጠና 1 ቁጥጥር ኃላፊ ኮማንድር ፍቃዱ ወንድም ናቸው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ለአገልግሎቱ ስኬታማነት በአዲስ አበባ ለሚገኙ ከ1 ሺህ 500 በላይ የትራፊክ ፖሊሶች ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል፡፡