በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፣ የካቲት 24/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።
"የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አስተዋጾ ተኪ የሆነ ተወዳዳሪ የለውም" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ በግብርና ላይ ያተኮረ ምክክር ዛሬ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የግብርና ዘርፉ ረጅም ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁንም አርሶ አደሩ ከበሬ ትከሻ ያልተላቀቀ አስተራረስ እየተከተለ ነው።
ዘርፉ የአገር የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ የአርሶ አደሩን ጉልበትና ድካም የሚቀንሱና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
"ክልሉ ሰፊ የሚለማ መሬት ስላለው ይህንኑ አቅም በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማምረት ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ "መንግስት ምርታማነትን ለማሳደግ አስፈላጊውንና የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው" ብለዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው "የአማራ ክልል ካለው የሚለማ መሬት አንፃር ሀያ እና አምሳ ትራክተር መጠየቅ አይመጥንም" ብለዋል።
በሜካናይዜሽን የታገዘ የምርት እድገት ለማምጣት ለዘርፉ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ ተቋም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በአመራሩ ችግር ካልሆነ በስተቀር ህዝቡ ሰርቶ ለመለወጥ ከልብ የሚጥርና የሚለፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥረቱ በቴክኖሎጂ መደገፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በክልሉ የተደራጀ የሜካናይዜሽን ተቋም መገንባት ግድ መሆንኑንና ለዚህም በመንግስት በኩል ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
"ክልሉ ሰፊ የሆነ የእርሻ ሃብት ባለቤት ቢሆንም ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ማዳበር ባለመቻሉ በምግብ እራስን መቻል አልተቻለም" ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው ናቸው።
በአማራ ክልል ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር ያላነስ የሚታረስ መሬት እንዳለ ገልጸው "ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ መላቀቅ ባለመቻሉ በምግብ እራስን ለመቻል እንደ ክልልም እንደሀገርም የተቀመጠውን ግብ ማሳካት አልተቻለም" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ የሆነ የአሰራር ለውጥ በማድረግ ደንበኞች የፋይናንስ አቅርቦት በወቅቱ የሚያገኙበት አሰራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባንኩ ባህር ዳር ዲስትሪክት ማናጀር አቶ አንማው ገዳሙ ናቸው።
"ብድሩ ቢፈቀድም ከአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አንጻር በፍጥነት "ኤል ሲ" የገንዘብ ክፍያ ማስተማመኛ ሰነድ የመክፈት ክፍተቶች ካልሆነ በስተቀር የብድር አሰጣጥ ሂደቱ የተሻሻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል።
ገበሬውን ከማወያየት፣ ከማሳመንና ከብድር ጀምሮ አስፈላጊ ድጋፎች ከተደረጉለት በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ የማምረት እድል እንዳለ የገለጹት ደግሞ አቶ አቶ ዓባይነህ መኮንን የተባሉ ባለሃብት ናቸው።
በምክክር መድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲና የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች እንዲሁም ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።