ቀጥታ፡

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በወሎ አካባቢ ለወደሙ ጤና ተቋማት የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ደሴ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) - "ምህረት ሜዲካል ሰፕላይ ግሩፕ" የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአሸባሪው ህወሓት ቡድን በወሎ አካባቢ ለወደሙ ጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለ60 ጤና ተቋማት እንዲከፋፈል ዛሬ ርክክብ ተደርጓል፡፡

በ"ምህረት ሜዲካል ሰፕላይ ግሩፕ" የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ማናጀር ወይዘሮ ፅዮን አላዛር በወቅቱ እንደገለጹት "በጦርነቱ የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋምና ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል" ብለዋል፡፡

ድርጅቱ በአማራ ክልል ለተጎዱ ጤና ተቋማት የሚውል 180 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ከዚህ ውስጥ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተውን በወሎ አካባቢ ለተጎዱ ጤና ተቋማት በወሎ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለ60 ጤና ተቋማት እንዲከፋፈል ዛሬ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አስረክበናል " ብለዋል ፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ የትምህርትና የጤና ተቋማት ጭምር በመዝረፍና በማውደም የታሪክ ጠባሳ አሳርፏል።

ዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ መውደሙንና መዘረፉን አስታውሰው በቅርቡ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ መማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው መልሶ እንዲቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ "ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በወሎ አካባቢ የወደሙ ጤና ተቋማት መልሰው ተቋቁመው ለህዝብ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ አየሰራን ነው" ብለዋል፡፡

"ማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ ራዕያችን በመሆኑ ህብረተሰቡ ከዩኒቨርሲቲው ብዙ ይጠብቃል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምንም እንኳ ችግር ላይ ብንሆንም በምንችለው አቅም ጤና ተቋማትን እናግዛለን" ሲሉም አክለዋል፡፡

የተለያዩ አጋር አካላት ለጤና ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ "ዛሬ ምህረት ሜዲካል ሰፕላይ ግሩፕ ያረገው ድጋፍ የዚሁ አካል ነው " ሲሉ አመልክተዋል፡፡

"ሰሞኑን ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎች ይደረጋሉ፣ በጣም ለተጎዱ ጤና ተቋማት በፍትሃዊ መንገድ እናሰራጫለን ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎችና 1 ሺህ 850 ጤና ኬላዎች በአሸባሪው ህወሓት ውድመትና ዝርፊያ የደረሰባቸው መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም