ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ አገር ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ አገር ናት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚሆኑ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ የልማት ዘርፍ ምክትል አምባሳደር ታይስ ዋውድስትራ ገለጹ።
ምክትል አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኔዘርላንድ እና ኢትዮጵያ ረዥም ጊዜያትን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አገራቱ በተለይ በግብርናው ዘርፍ በጋራ ይሰራሉ ነው ያሉት፡፡
ኔዘርላንድ በኢትዮጵያ ሰፊ ኢንቨስትመንት ካላቸው አገራት ተርታ እንደምትሰለፍም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ብቻ ሳትሆን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች ያሏት አገር መሆኗንም ነው ያነሱት፡፡
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ በርካታ የሰው ኃይል እንዳላት ጠቅሰው፤ ይህም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማውጣት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች መልካም እድል ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ የሚሆኑ የኔዘርላንድስ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ ወተትና ወተት ተዋጽኦ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማውጣት እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ ግዙፍ የንግድ አጋር መሆኗን ያነሱት ምክትል አምባሳደሩ፤ አገራቸው የአበባና የቡና ምርት ከኢትዮጵያ እንደምታስገባም ተናግረዋል።
ሁለቱ አገሮች በቀጣይ ከግብርና በተጨማሪ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ በሚያስችሉ የሎጅስቲክስ ዘርፎች ላይ በትብብር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለገበያ ተደራሽ እንዲሆን የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግም ነው የገለጹት፡፡