ቀጥታ፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ደረጃዎች አተገባበር ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፣  የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) እንደ ሃገር የሚወጡ ደረጃዎች አተገባበር ላይ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በማርና ማር ውጤቶች እና ጨርቃጨርቅ ዘርፍ ለተሰማሩ አምራቾች፣ ማህበራትና ባለድርሻ አካላት በወጡ ደረጃዎች አተገባበር ዙሪያ  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ  በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ   እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ  አለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ደረጃ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች አባል በመሆኑ የሚዘጋጁ ደረጃዎች ተቀባይነት ያላቸው ናቸው።

ደረጃ ለአንድ ሃገር ኢኮኖሚ፣ እድገትና ተወዳዳሪነት ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ደረጃዎችን ማስጠበቅ የምርቱን ተቀባይነትና በተቀባይ ሃገራት መካከል አመኔታ የሚያጎለብት መሆኑንም ተናግረዋል።

አለም አቀፍ ሁኔታው ደረጃዎችን እንድናወጣና እንድንተገበር በሚያስገድድበት በአሁን ወቅት እንደ ሀገር በደረጃ ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ ወደ ኋላ አስቀርቶናል ነው ያሉት።

እንደ ሃገር የሚወጡ ደረጃዎች በአምራቾች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ተጠቃሚዎች በተገቢው አለመተግበራቸውን ገልጸዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለያዩ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላትን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፤  የሃገሪቱ ምርቶችና አገልግሎቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ደረጃ ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ፤ ከምግብ ደህንነት ጋር ተያይዞ ሃገራት የዜጎቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ  ደረጃዎችን እንደሚቀይሩና የነበሩትንም የማሻሻል ስራ በየጊዜው እንደሚከናወን ተናግረዋል።

እንደ ሃገር ከ11 ሺህ በላይ ደረጃዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አምራቹና ተጠቃሚው ግን ደረጃዎችን አውቆ ከመተግበር አንጻር ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ደረጃዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉት ማንን እንደሆነ ካለማወቅ የሚመነጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለማቃለል በየዘርፉ የግንዛቤ ስራ በመስራት አለም ላይ ተፈላጊ ምርት ማምረት ያስፈልጋል ብለዋል።

ደረጃ ከአለም ጋር የምንግባባበት ትልቁ መሳሪያ ነው ያሉት አቶ ቦንሳ፤ ኢንስቲዩቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የስልጠና ማዕከል ገንብቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር የፕሮጀክት ማናጀር  አቶ ያሬድ ብርሃኔ በበኩላቸው፤ በሃገር ደረጃ የፀደቁ ደረጃዎች አተገባበር ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት እንደ ማህበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በማጥናት ለመንግስት ማቅረብና የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውንም በመለየት አምራቾች ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ምርት እንዲያመርቱ በትብበር እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የግንዛቤ ስልጠናው በአምራቾች ዘንድ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ጉልህ ሚና እንዳለውና በየደረጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ልማት ኢንሰቲትዩት የማርና ሰም ማቀነባበርና ምርምር ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ የሺጥላ እሸቴ ፤ በማር ምርት ላይ የእሴት ሰንሰለቱን የጠበቁ ደረጃዎች ወጥተው የጸደቁ ቢሆንም አተገባበሩ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት መድረኩ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ደረጃውን በተገቢው መተግበር ልማቱን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ለተጠቃሚው  ደህንነቱን የጠበቀ ምርት ለማቅረብ ብሎም ለውጭ ከሚያቀርቡት ጋር ለመወዳደር እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ማር ከቀፎ ከወጣ በኋላ ባለው ሂደት ጥራቱን የሚያጓድሉ ነገሮችን መቀነስ አምራቹን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም