የሲዳማ ክልል ውጤታማ የሰላምና ደህንነት ተግባር ማከናወኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ክልል ውጤታማ የሰላምና ደህንነት ተግባር ማከናወኑን ገለጸ
ሀዋሳ፣ የካቲት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ የፀጥታ ስራዎች መከናወናቸውን አስታወቀ።
ለክልሉ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊስ አመራርና አባላት በወቅትዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ በመድረኩ እንዳሉት፤ በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅር ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል።
የጋራ እቅድ በማቀድና ለፖሊስ ኃይል በየደረጃው ስልጠና በመስጠት የተሰራው ስራ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ መፍጠር ማስቻሉንም ተናግረዋል።
የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል የፖሊስ አባላትና አመራሮች በዘርፉ የላቀ ለውጥ ለማምጣት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።
የፀጥታ መዋቅሩ ያከናወናቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀመጥ መድረኩ እንደተመቻቸ የገለጹት ሃላፊው፤ ተመሳሳይ መድረክ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተስፋዬ ቱንገሞ በበኩላቸው በክልሉ የህግ የበላይነት በመረጋገጡ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን ተናግረዋል።
የተገኘውን ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የፀጥታ ኃይሉ የሚሰጠውን ግዳጅና ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት የሚያግዙ ስራዎች እንደሚከናወኑም አመልክተው፤ ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ያለውን ጥምረት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።