ከአባቶች የተረከብናትን ነጻ ሀገር አንድነቷን ጠብቀን የማቆየት ሃላፊነት አለብን-ወጣቶች

85

ባህር ዳር ፤ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) አባቶቻችን በመስዋዕትነት ያስረከቡንን ነጻ ሀገር በዘርና ጎጥ ሳንከፋፈል አንድነቷን በማስጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማቆየት የኛ ሃላፊነት ነው ይላሉ በባህርዳር ከተማ የዓድዋ ድል በዓል ታዳሚ ወጣቶች ።

ነዋሪነቱን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረገው ወጣት የፍቅርሰው አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ቅድመ አያቶች  ትልቅ ዋጋ ከፍለው ነው ኢትዮጵያን ያቆዩት።

የዓድዋን ድል 126ኛ ዓመት በዓል  በነፃነት ማክበር የተቻለው ጀግኖች አባቶች ትልቅ ታሪክ ሰርተውና የሕይወት ዋጋ ከፍለው ከነጭ ወራሪ ነጻ   ስላስረከቡን  ነው ሲል ተናግሯል።

"የሀገርን ክብርና ነጻነት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እኛም የአባቶቻችንን አደራ ተቀብለናል፤ ከእነሱ ደማቅና አኩሪ ታሪክ በመማር የእኛን አዲሰ ታሪክ ልንሰራ ይገባል" ብሏል።

በተለይ የእዚህ ዘመን ወጣቶች በዘርና ጎጥ ሳንከፋፈል ቀደምት ጀግኖች አባቶች በመስዋዕትነት ያቆይዋትን  ኢትዮጵያን ክብሯን በማስጠበቅ ለትውልድ ማስረከብ የኛ ሃላፊነት ነው ሲል ገልጿል ወጣት የፍቅርሰው።

"ዓድዋ ለእኔ የቀደሙ አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬ በነፃነት ቆሜ እንድሄድ መሰረት የተጣለበት ትልቅ የድል ቀን ነው" ያለችው ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ገነት ተመስገን ናት።

ድሉ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ በዓለም የሚገኙ መላ ጥቁር ህዝቦች ከባርነት ተላቀው ነፃነትን እንዲጎናፀፉ ምክንያት መሆኑን ተናግራለች።

ጀግኖች አባቶች ያወረሱንን አኩሪ ገድል፣ አንድነት እና የሀገር ፍቅር በአግባቡ ጠብቀንና ተንከባክበን ማስቀጠል ከእኛ የዘመኑ ትውልድ ይጠበቃል" ብላለች።

ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ የታፈረች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረን በመስራት ሌላ የአድዋ ድል ማስመዝገብ እንደሚገባም አመልክታለች።

ወጣት አሜን አያሌው በበኩሏ፣ የዓድዋ ድል ከአባቶቻችን አደራ የተቀበልንበትና አይቻልምን የሰበርንበት ታሪካዊ ቀን   ነው ስትል ገለጻችው።

እንደ ወጣቷ ገለጻ፤ ጀግኖች አባቶች በደማቁ  የጻፉትን አኩሪ ታሪክ ማስቀጠል ከዚህ ዘመን ትውልድ የሚጠበቅ ነው።

ወጣቶቹ የሀገር አንድነትና ሰላም በማስጠበቅ በተሰማሩበት ሙያ ውጤታማ በመሆን የቀደሙ አባቶችን ወርቃማ ታሪክ በልማት ለመድገም እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

126ኛው  ዓመት የዓድዋ የድል በአል  በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች  ትናንት በድምቀት መከበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም