በአገራዊ ምክክሩ ሉዓላዊነትና አንድነትን የሚያጸኑ ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ አዲስ ታሪክ መጻፍ ይገባል

70

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገራዊ ምክክሩ ሉዓላዊነትና አንድነትን የሚያጸኑ ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ መጻፍ ይገባል ሲሉ የታሪክ ምሁራን አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር መድረክ በንግግርና በመግባባት ላይ በመመስረት አገርን በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር መልካም የታሪክ አጋጣሚ ስለመሆኑም ምሁራኑ ጠቁመዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አቶ አቤል ጫላ፤  አገራዊ ምክክሩ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን ይናገራሉ።

የአገራቸውን ሰላም ያጸኑ፣ የዜጎቻቸውን ብልጽግና እውን ያደረጉ አገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአንድ አገር ልማት፣ እድገትና ብልጽግና መረጋገጥ የሰላም ዋጋ ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከምንም በማስቀደም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ አገራዊ ምክክር በማድረግ በልዩነቶች ላይ መነጋገር፤ በቅራኔዎች ላይ እርቅ መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሊካሄድ በዝግጅት ላይ በሚገኘው አገራዊ ምክክር ተነጋግሮ በመግባባት የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያጎላ ሥራ በመሥራት የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በአገራዊ ምክክሩ ሉዓላዊነትና አንድነትን የሚያጸኑ ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ መጻፍ ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ደቻሳ አበበ፤ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ ተቀራርበው በመምከር የአገራቸውን መሰረት ማጽናት አለባቸው ብለዋል።

በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለምክክርና ለንግግር በመዘጋጀት ብሄርና ሃይማኖት ሳይገድበን ተቀራርበን ተነጋግረን በመግባባት ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች አገር እንገንባ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ ምክክሩን የሚያስተባብሩ 11 ኮሚሽነሮችን ሹመት ማጽደቁ ይታወሳል።

የኮሚሽኑ መቋቋም መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች ሌሎች  የህብረተሰብ ክፍሎች ተቀራራቢና ለአገራዊ አንድነት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ማድረግ የአካታች አገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ግብ እንደሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተደንግጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም