በሐረሪ ክልል ለጎብኚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ የአንድ ማዕከል የክፍያ ሥርዓት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ለጎብኚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ የአንድ ማዕከል የክፍያ ሥርዓት ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ለጎብኚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል የአንድ ማዕከል የክፍያ ሥርዓት መጀመሩን የክልሉ ባህል፣ ቅርስ ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።
የክልሉ ባህል፣ ቅርስ ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለድ አብዶሽ እንደገለጹት፤ በክልሉ የዓለም ቅርስ የሆነውን የጀጎል ግንብ ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ።
እነዚህን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ መስህቦች ለመጎብኘት በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የውጭ አገር ቱሪስቶችና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው እንደሚያቀኑ ጠቁመዋል።
በክልሉ የቱሪስት መስህብ መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ከማድረግ ጀምሮ በዘርፉ ከአገልግሎት አሰጣት ጋር የተያያዙ አሰራሮችን የማሻሻል ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቱሪስቶች በመዳረሻ ሥፍራዎች ላይ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል የአንድ ማዕከል የክፍያ ሥርዓት መጀመሩን ጠቁመዋል።
የክፍያ ሥርዓቱ ቱሪስቶች ወደ አካባቢው ለጉብኝት በሚመጡበት ጊዜ በየመዳረሻ ሥፍራዎች ማዕከላት ክፍያ መፈጸም ሳይጠበቅባቸው አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ አሁን ካሉት መዳረሻዎች በተጨማሪ አዳዲስ መዳረሻዎችን የማልማትና ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ለአብነትም በአካባቢው በርካታ የአርጎባ ብሔረሰብ የሚኖርባትና "ኮረሚ መንደር" በመባል የምትታወቀውን ጥንታዊ ሥፍራ የማልማትና የማጠናከር ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም አዲስ የኢትዮጵያን ኢስላማዊ የሥነ-ጽሁፍና የእደ ጥበብ ውጤቶችን የያዘ ሙዚየም ግንባታ እየተጠናቀቀ ሲሆን ይህም በቅርቡ ለኅዝብ ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በሐረሪ ክልል በቱሪስቶች ከሚጎበኙት ቅርሶች መካከል በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታሪካዊ የጀጎል ግንብና በውስጡ የሚገኙ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና አምስቱ መግቢያ በሮች ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቦ መኖሪያ ቤት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ ሙዚየሞችና የጅብ ምገባ ትርዒት ተጠቃሽ ናቸው።